ሰላም እና እርቅ ለማወረድ አባታዊ ኃላፊነታቸዉን በመወጣት ላይ የነበሩ አባት በታጣቂዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል ሰላም ካውንስል ገለጸ።

31
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰላም ካውንስል የሰሜን ጎጃም ዞን የሰላም ካውንስል መሪ የነበሩት መልዓከ ምህረት ነቃጥበብ ገነት በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት በእርቅ እንዲፈታ ሲሠሩ እንደነበር ካውንስሉ ገልጿል።
ችግሮች በሰላም እንዲፈቱም በሕዝባዊ ስብሰባዎች እና በሰላም ጉባኤዎች ላይ ሲያስተምሩም ነበር ተብሏል። መልዓከ ምህረት ነቃጥበብ የታጠቁ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር እንዲወያዩ፣ ሰላም እንዲሰፍን እና የክልሉ ሕዝብ ስቃይም እንዲያበቃ ሲማጸኑ መቆየታቸውን ካውንስሉ በመግለጫው አንስቷል። ይሁን እንጅ ይህንን የሰላም ዓላማ የሚጻረሩ አካላት ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም ምሽት ላይ እኒህ አባት ከሚያገለግሉበት ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ታጥቀው በመግባት አፍነው ወስደዋቸዋል። ክብራቸውን በማይመጥን መልኩ ዳህና ማርያም ወደተባለው የታጣቂዎች ምሽግ በመውሰድም ለስቃይ ሲዳርጓቸው መቆየታቸውን ካውንስሉ ገልጿል። ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም ደግሞ እኒህን ሰላም ወዳድ አባት በግፍ መግደላቸው ታውቋል ብሏል።
መልዓከ ሰላም ነቃጥበብ ገነት በአድባራት እና ገዳማት ለ17 ዓመታት ያገለገሉ መንፈሳዊ አባት፤ ስለሀገርና ስለሕዝባቸው ወቅታዊ ችግርም መፍትሔ ለመፈለግ የበኩላቸውን ጥረት የሚያደርጉ ነበሩ ብሏል ካውንስሉ በመግለጫው። የእኒህ አባት ግድያ ካውንስሉን ሰላምን ለማስፈን ከሚሠራው አላማው ለአፍታም እንኳን ወደኃላ እንደማያደርገው አስታውቋል። በሰላም ወዳዱ አባት ግድያ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናልም ብሏል በመግለጫው። ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም ደቡብ አቸፈር ዱርቤቴ ከተማ በሚገኘው የሟች የመኖሪያ ቤት በመገኘት የምስለ ቀብር ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድም ተገልጿል። ካውንስሉ ለአሚኮ በላከው መግለጫ የሰላም ዋጋ በመስዋዕትነት የሚመጣ መኾኑን ትምህርት ለመስጠት በጋራ መሰለፍ እንደሚገባም ጥሪ አቅርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
Previous articleትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ነው፤ መምህራን ደግሞ የሁሉም ናቸው!
Next articleከ6ሺህ በላይ ተማሪዎችን በፓይለት ምዝገባ ሂደት ለመመዝገብ ማቀዱን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።