ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ነው፤ መምህራን ደግሞ የሁሉም ናቸው!

17
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2018 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር እንደ ክልል አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
በሚፈጠሩ የሕዝብ መድረኮች ላይ የሚታየው የሕዝብ ስሜትም ተስፍ ሰጭ እንደኾነ ቢሮው ገልጿል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደምስ እንድሪስ ክልሉ የገጠመውን የትምህርት ስብራት ችግር ለመጠገን የጋራ ኀላፊነትን ይጠይቃል ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርቱ ላይ የደረሠው ጉዳት የክልሉን ተወዳዳሪነት አደጋ ውስጥ ያስገባ እንደኾነም ገልጸዋል። ከዚህ ችግር ለመውጣት ቢሮው በዚህ ዓመት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል። የመምህራንን አቅም የመገንባት ሥራ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ እንደኾነም ነው የተናገሩት።
ከ10 ሺህ በላይ የሚኾኑ የአንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች እንዲኹም 24 ሺህ የሚጠጉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎችን የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
ሥልጠናው ከነበረው የሥነ ልቦና ጭንቀት የሚያወጣ እና በተነሳሽነት ለትውልድ ግንባታ እንዲተጉ ታሳቢ ተደርጎ ተሰጥቷል ብለዋል። ባለፈው ዓመት በጸጥታ ችግሩ ምክንያት እንግልት እና ስቃይ ከደረሰባቸው አካላት መካከል የቀለም አባት የኾኑት መምህራን እንደሚገኙበት ምክትል ቢሮ ኀላፊው አስታውሰዋል።
አንድ ደርዘን ለአንድ ተማሪ ንቅናቄ በክረምቱ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ውስጥ እንደኾነም አንስተዋል። በዚህ አንድ ወር ውስጥ 78 ሺህ 578 ደርዘን ደብተር እና ሌሎች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ ተሠብሥቧል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡም በቀናኢነት ተሳትፏል ብለዋል።
ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በትኩረት ሲሰጥ እንደቆየም ተናግረዋል። በዚህም 3ሺህ 738 በጎ ፈቃደኞች በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ተሳትፈዋል ነው ያሉት። 567 የአንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤቶች ላይ 53 ሺህ 494 ለሚኾኑ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷቸዋልም ብለዋል። 146 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይም ተግባሩ እንደተከናወነ አንስተዋል።
እየተደረገ ያለው የንቅናቄ ሥራ ካለፉት ዓመታት ለየት የሚያደርገው የደረሰው የትምህርት ስብራት ሊበቃ ይገባል በሚል እሳቤ መተግበሩ ነው ብለዋል። ትምህርትን መጉዳት ዞሮ የሚጎዳው የክልሉን ማኅበረሰብ መጻኢ እጣ ፈንታ እንደኾነ ነው አቶ ደምስ የገለጹት። በጊዜ ሂደት ክልሉ የተማረ የሰው ኅይል እንዳያጣ ችግሩ ሊበቃ ይገባል በሚል መንፈስ ኅብረተሠቡ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ነው ያሉት። በቀጣይ 2018 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚኾኑ ተማሪዎችን ለማስተማር እንደ ክልል ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል። በሚፈጠሩ የሕዝብ መድረኾች ላይ የሚታየው የሕዝብ ስሜትም ተስፍ ሰጭ እንደኾነ ምክትል ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
መላው የክልሉን ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን በአጠቃላይ የሚመለከታቸው ሁሉ የዚህ ታላቅ ሕዝብ ችግር ሊያማቸው ይገባል ብለዋል። ነሐሴ19/2017 ዓ.ም የአንድ ቀን የንቅናቄ ምዝገባ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ትበይን ባንቲሁን ባለፈው ዓመት የነበርው የመማር ማስተማር ተግባር ፈታኝ እንደነበር አስታውሰዋል። ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡትን ጨምሮ ከፍተኛ የተማሪ ቁጥር አስተናግደን ከርመናል ነው ያሉት። ከ131 ሺህ በላይ ተማሪ በከተማዋ ባሉ ትምህርት ቤቶች አስተናግደን ከርመናል ብለዋል። ያም ኾኖ ብዙ ልጆችን ያስተማርንበት እና የህሊና ትርፍም ያገኘንበት ዓመት ነበር ነው ያሉት።
ራሳቸውን ችግር ውስጥ አስገብተው የትውልድ ነገር ገዷቸው ሲያስተምሩ የከረሙ መምህራን ክብር ይገባቸዋል ብለዋል ምክትል መምሪያ ኀላፊዋ። ትምህርትን ለማስቀጠል ሕይወታቸውን ያጡ መምህራንን አስታውሰዋል። ይህ የኾነው ለሙያው ባላቸው ክብር በመኾኑ ነው ብለዋል። ሰው ካልተሠራ ሀገር የለም ነው ያሉት። ትምህርትን ማስቀጠል የቀጣይ ዜጋን መሥራት እንደኾነ ነው የገለጹት። መሬት ብቻውን ሀገር አይኾንም። ጋራው ሸንተረሩ ያለ ዜጋ ከንቱ ነውና ትምህርት ላይ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ዜጋን ማስቀጠል የሚፈልጉ መምህራንን ልንቆምላቸው ይገባል ነው ያሉት። የ2017 በጀት ዓመትን ገምግመው በዚህ ዓመት የተሻለ ለማሳለጥ በቁርጠኝነት ወደ ተግባር መግባታቸውንም ወይዘሮ ትበይን ገልጸዋል። አቶ ሲሳይ ጌትነት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሱፐርቫይዘር ናቸው። መምህርነት ታላቅ ሙያ ኾኖ ሳለ ባለፉት ጊዜያት በወንድሞቻችን ላይ የማይገባ ተግባር ሲፈጸም ቆይቷል ነው ያሉት። ትውልድን ከመገንባት በላይ የሚከበር ተግባር የለም፤ መምህራን ሊከበሩ ይገባል ብለዋል። “ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ነው፤ አስተማሪዎች ደግሞ የሁሉም ናቸው” ነው ያሉት። በቀጣይ የዜጋ ግንባታ የማስተማር ተግባራቸውን በቁርጠኝነት እንደሚያከናውኑም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየአሚኮ የቴክኖሎጂ ጉዞ “ከክር እስከ ኦቪቫን”
Next articleሰላም እና እርቅ ለማወረድ አባታዊ ኃላፊነታቸዉን በመወጣት ላይ የነበሩ አባት በታጣቂዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል ሰላም ካውንስል ገለጸ።