
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው አብመድ የዛሬው አሚኮ በጥቂት ጋዜጠኞች እና በውስን ቴክኖሎጅ መረጃን ለኅብረተሰቡ በማድረስ በ1987 ዓ.ም ነው ሥራውን የጀመረው።
ያኔ ሥራውን ሲጀምር በቂ ቴክኖሎጅ አልነበረም፣ ሃሳብ እንጅ በቂ የመሣሪያ ቁሳቁስ አልነበረም፣ ልፋት እንጂ ምቾት አይታሰብም፣ ብዙ ልፋት፣ ብዙ ውጣ ውረድ ታልፏል። በዚህ ጉዞ ብርታት እንጂ ድካም ቦታ አልነበረውም። አርቆ አሳቢዎች ራዕይ ሰንቀው፣ ግብ አስቀምጠው በጽናት ተጉዘዋል፤ የያኔውን ልፋት ሳይኾን ዛሬን አስበው ተግተዋል፤ ጽናትን አስተምረው ለዛሬው ትውልድ በአደራ አስረክበዋል፤ ነገን አሻግረው አልመው ሠርተዋል የዛሬ 30 ዓመት የአሚኮ መሥራች ቤተሰቦች። አሚኮ በበኩር ጋዜጣ ተነስቶ በሂደት ደግሞ በመደበኛ ሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በኤፍ ኤም፣ በጋዜጦች እና በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች አድማሱን እያሰፋ እነኾ 30 ዓመታትን በጽናት አሳልፏል።
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥልጠናና ምርምር ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ጌታቸው መሐሪ በዚህ አንጋፋ ተቋም በተለያዩ የሥራ ክፍሎች በማገልገል 30 ዓመታትን አብረው ዘልቀዋል። በተቋሙ ከካሜራ ባለሙያነት እስከ ሥርጭት ተቆጣጣሪነት እና ዳይሬክተርነት በደረሰ የሥራ ድርሻ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። ሚዲያው ሥራ ሲጀምር ኋላቀር፣ አድካሚ እና አሰልቺ የኾነ ቴክኖሎጅ በመጠቀም እንደነበር ነው የገለጹት። በካሴት ዴክ እና ቪ ቺ ኤስ በሚባሉት በአናሎግ የቀረጻ እና የቅንብር መሣሪያዎች እየተሠራ የቆየበትን ጊዜም አስታውሰዋል።
በዚህም ምክንያት የድምጽ እና የምስል ጥራት ችግር ይገጥም እንደነበር ተናግረዋል። በተለይም በመስክ በሚሠሩ የቀረጻ ሥራዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
የመሠረተ ልማት አለመሟላት ከነበረው ኋላ ቀር ቴክኖሎጅ ጋር ተዳምሮ በመስክ የተቀረጸ ሥራን ተመልሰን ወደ ቢሮ በመምጣት ነበር የሚሠራው ይላሉ። የሚዲያ ቴክኖሎጅው ኋላ ቀር ከመኾኑ የተነሳ በተለይም ሬዲዮ ላይ የቴፕ ካሴት እየተቆረጠ ኤዲት የማድረግ እና የማስተካከል ሥራ ይሠራ ነበር ነው ያሉት። ከዞን ዘገባዎች የሚሠሩ ዜናዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ያደርገው እንደነበርም አንስተዋል። ዜናው በዘጋቢዎች ተሠርቶ የሚላከው በመገናኛ ሬዲዩ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ከዞን የተላከውን ማዕከሉ ደግም ከሬዲዮ በማዳመጥ በቴፕ ሪከርድ ይደረጋል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ጹሑፍ ተቀይሮ አርትኦት ተሠርቶ ለስርጭት ይላክ እንደነበር ገልጸዋል።
ድምጽ ተቀርጾ ሲያስቸግር ክሩ እየተቆረጠ እንደገና በፕላስተር በማያያዝ ይሠራ እንደነበር ነው ያስታወሱት። በዚህ ውጣ ውረድ ዜና ተሠርቶ ለማስተናገድ በአማካይ እስከ ስድስት ቀናት ይፈጅ እንደነበር ነው የሚገልጹት። በዚያ ዘመን አንድ ዜና ለማስነበብ እንኳን ከዛፍ ስር ወስደን አስነብበን እና ቀርጸን ነበር ለኢቲቪ የምንልክ ይላሉ 30 ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዘው ሲያስታውሱ። እንዲህም ለፍተን የሠራነው ሥራ በቂ ቴክኖሎጅ ስላልነበረ ሳይተላለፍ የሚቀርበት አጋጣሚዎችም ነበሩ ይላሉ። አውሮፕላን ጥሎ ከሄደ የተለፋበት ዜና ይታጠፍብን ነበር ነው የሚሉት።
በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ግን ለታሪክ የሚቀመጥ፣ ለትውልድ የሚተላለፍ፣ የክልሉን ገጽታ የሚያሳይ ሥራ መሠራቱን በኩራት ይናገራሉ። በቂ የቴክኖሎጅ ሥልጠና አለመኖሩም ሌላው ፈተና እንደነበር ጠቁመዋል። አብዛኛው ሥራ በራስ ጥረት ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደነበርም አስታውሰዋል። አሁን ላይ ቴክኖሎጅውን በመጠቀምም አሚኮ በሚያዘጋጀው የአቅም መገንቢያ ሥልጠናዎች የቴክኖሎጅ አቅምን ማሳደግ ይቻላል ነው ያሉት። ዛሬ ቴክኖሎጅ አድጓል፣ የድጅታል አማራጮች መጥተዋል፣ አሚኮም ይህንን ቴክኖሎጅ እየተጠቀመ ይገኛል ብለዋል። አሚኮ ዘመኑ የፈጠራቸውን የሚዲያ ቴክኖሎጅ እየተጠቀመ ይገኛል ነው ያሉት።
አሚኮ በአሁኑ ሰዓት ሳተላይት ይጠቀማል፣ የቀጥታ ሥርጭት መምራት እና ማስተላለፍ ችሏል፣ ዘመናዊ ስቱዲዮ ገንብቷል፣ ዲ ኤን ኤም ጅ፣ ኤስ ኤም ጅ እና ሌሎችንም የድጅታል ቴክኖሎጅዎችን እየተጠቀመ ይገኛል ብለዋል።የአሚኮ የቴክኖሎጅ ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ ተሾመ ውዱ አሚኮ በመጀመሪያ ከኢቲቪ ሳምንታዊ የአየር ሰዓት በመግዛት ውስን በኾነ ቴክኖሎጅ ሚዲያ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። በዚያን ወቅት ፕሮግራም ሠርቶ በካሴት በመላክ ይሠራ እንደነበርም ገልጸዋል። በሂደትም አሚኮ የቀረጻ፣ የቅንብር እና የሥርጭት መሣሪያዎችን ከአናሎግ ወደ ድጅታል ቴክኖሎጅ አሳድጓል፤ ዘመኑ የደረሰበትን እና የተሻለ ቴክኖሎጅ እየተጠቀመ መኾኑን ነው የገለጹት።
የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ሥርጭቱንም በማሳደግ ወደ ቋሚ ሥርጭት መሸጋገሩን ተናግረዋል። በአኹኑ ጊዜ አሚኮ የቀረጻ ቴክኖሎጅዎችንም በማሳደግ ዘመናዊ የመስክ ቀረጻ እና ሥርጭት ለመሥራት የሚያስችል የኦቪቫን ቴክኖሎጅን ሥራ ላይ አውሏል ብለዋል። ቴክኖሎጅ ፈጣን እና ተለዋዋጭ የኾነ ለውጥ የሚታይበት ቢኾንም ተወዳዳሪነትን መሠረት ያደረጉ የሚዲያ ቴክኖሎጅ መሠረተ ልማቶችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት። በአማርኛ እና በኅብር የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የ24 ሰዓት የሥርጭት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም ሙሉ የኤች ዲ የማሠራጫ ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። በጥቂት ባለሙያዎች እና በካሴት ክር የጀመረው አሚኮ በ30 ዓመታት ጉዞው ዓለም የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጅ የኦቪቫን ባለቤት በመኾን ግዙፍ ተቋም ኾኗል ነው ያሉት። በቀጣይም አኹን ያሉትን ቴክኖሎጅዎች ደረጃዎችን በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳሪ የሚያደርጉ ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን ለመጠቀም በሰፊው ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን