በኩር በ30 ዓመታት

8
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የሕትመት ብዙኀን መገናኛ ዘርፉን ከተቀላቀሉት ክልላዊ ተቋማት መካከል ቀዳሚው እና አንዱ አሚኮ ነው፡፡
ድርጅቱ በአዋጅ ቁጥር 56/1993 ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ ነበር በኩርን በሕትመት ዘርፉ ለአንባቢያን ማቅረብ የጀመረው፡፡ በአሚኮ ታሪክ ቀዳሚውን ቦታ የምትይዘው በየሳምንቱ እየታተመች ለንባብ የምትበቃው በኩር ስያሜዋ የግዕዝ ቃል ሲኾን ትርጓሜውም የመጀመሪያ ወይም ቀዳሚ ማለት ነው ይላል ከበኩር ጋዜጣ መሥራች ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የኾነው የበኩር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ፈንቴ፡፡
በኩር በቋሚነት እየታተመች ለአንባቢያን ተደራሽ የኾነችው ታኅሣሥ 7/1987 ዓ.ም ሳምንታዊ የሐሙስ ጋዜጣ ኾና ነበር ብሏል፡ በመጀመሪያ አካባቢ በሳምንት 4 ሺህ ኮፒ ያክል እየታተመች ለስርጭት ትበቃ የነበረችው በኩር ጋዜጣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን እና ባሕልና ስፖርት አምዶችን አካትታ ትይዝ ነበር፡፡በመጀመሪያ በስምንት ገጽ የተጀመረችው በኩር ጋዜጣ የተነባቢነት ደረጃዋ እና ተወዳጅነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጋዜጠኛው ተናግሯል፡ በወቅቱ የነበረውን የቴክኖሎጅ እና የተሟላ ግብዓት አቅርቦት ውስንነት በመቋቋም አሁን ካለችበት ደረጃ እንድትደርስ በጊዜው የነበሩ ጋዜጠኞች ድርሻ ከፍተኛ ነበር ብሏል ጋዜጠኛ ጌታቸው።
ሌላው ቀርቶ ለጋዜጣዋ አገልግሎት ይሰጥ ለነበረው አንድ ኮምፒውተር እንኳን በወቅቱ ከነበሩት ሠራተኞች መካከል የኮምፒውተር ጽሕፈት የሚችል ሰው ባለመኖሩ የጽሕፈት ባለሙያ ከአዲስ አበባ እንዳስመጡ ያስታውሳል፡፡ የጽሑፍ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላም የተጻፈውን በመቁረጥ እና በታዳሚው ላይ የገጹን ንድፍ፣ ቅርጽ እና የቅንብር ሥራውን በማከናወን በሙጫ እያጣበቁ ወደ አዲስ አበባ ማተሚያ ቤት በመላክ ለህትመት ያበቁ እንደነበርም ነው የተናገረው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምላጭ፣ ብርሃን አስተላላፊ ቁስ እና ሌሎች ግብዓቶችን በመጠቀም ኋላቀር እና አድካሚ በኾነ አሠራር ይሠሩ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ይህንን ሥራ ሢሠሩ ጋዜጠኛ የመኾን ብርቱ ፍላጎት ኖሯቸው እንጅ ከመካከላቸው በጋዜጠኝነት የተማረ ሰው እንዳልነበረ ጋዜጠኛ ጌታቸው አብራርቷል። በወቅቱ ከነበረው የቴክኖሎጅ ውስንነት እና የአቅርቦት አለመሟላት ጋር ተያይዞ ሥራው ለዘጋቢዎች ትልቅ ፈተና ነበር ብሏል፡፡
በኩርን ሲጀምሩ ከምንም በመነሳት ብዙ ችግሮችን አሳልፈው እንደኾነ ገልጾ ዛሬ ላይ አሚኮ በ30 ዓመት ሂደቱ እጅግ ዘመናዊ በኾነ የመገናኛ ብዙኀን ቴክኖሎጅ በመደገፍ የሕትመት ሥራውን እንደሚሠሩ ነው የተናገረው፡፡ አሁን ላይ ጋዜጠኞች ሙያዊ ኀላፊነታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ስለመደረጉም ጠቁሟል፡፡
እዚሁ ቁጭ ብለን ሠርተን ያሳተምነውን ዕትም በሰከንዶች ወደ ዓለም በማሰራጨት ግብረ መልስ የምናገኝበት ተቋም ኾኗልም ብሏል፡፡ “ለኔ ዛሬ ላይ ኾኘ ይህንን በማየቴ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ዕድለኛ ነኝም” ብሏል፡፡ በኩር ለአሚኮ መመሥረት መነሻ ናት ያለው ጋዜጠኛው በወቅቱ በበኩር ዕትም ምክንያትም ተቋሙ እንዲታወቅ ምክንያት ኾኗልም ሲል ገልጾታል፡፡ በአሚኮ የ30 ዓመት ዕድሜ ለውጥ በኩር ከጥቁር እና ነጭ ቀለም ወጥታ ባለ ቀለም መኾን ስለመብቃቷም አስረድቷል። በኩር በትምህርት ብቁ በኾኑ ጋዜጠኞች እና በቴክኖሎጅ በመደገፍ ችግሮች ሳይበግሯት በማኅበራዊ ሚዲያው በደቂቃዎች ውስጥ ተደራሽ እንደኾነችም ጠቁሟል፡፡
በኩር ሙስናን በመታገል፣ የክልሉን ባሕል እና ትውፊት በማስተዋወቅ፣ የአርሶ አደሩ ሕይዎት እንዲለወጥ እና ትርፍ አምራች የሚኾንበትን መንገድ በማሳየት፣ ማኅበረሰቡ ከተለያዩ በሽታዎች እራሱን እንዲጠብቅ፣ የተለያዩ የአዝዕርት በሽታዎች ሲከሰቱ ቀድሞ የመከላከል ሥራ እንዲሠራ የተለያዩ መረጃዎችን በወቅቱ በማድረስ በኩል ብዙ መረጃዎችን አስተላልፋለች ብሏል፡፡ በኩር ታሪክን ሰንዶ በማስቀመጥ በኩልም ያበረከተችው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ባይ ነው። ማንም አካል ቆየት ያሉ መረጃዎችን ቢፈልግ ያለፉትን መዛግብት አገላብጦ ለማጣቀሻነት መጠቀም ይችላል ነው ያለው፡፡ በበኩር ፈር ቀዳጅነት የተጀመረው የድርጅቱ የሕትመት ሚዲያ በሦሥቱም ቋንቋዎች ማለትም በቺርቤዋ፣ በአዊኛ እና በሂርኮ ጋዜጦች ለአንባብያን ተደራሽ እየኾኑ እንደሚገኙም አስረድቷል፡፡ ይህም ለክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ ተደራሲያን አማራጭ የመረጃ ምንጮች ናቸው ብሏል፡፡
ዘጋቢ: ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአገው ባሕል እና ትውፊትን ለመግለጥ አሚኮ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
Next articleበሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ከ5 ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት የልደት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ እየተሠራ ነው።