
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የአዊ ብሔረሰብ አንዱ መለያ እንዲኾን ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተለይ ማኅበሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ወለሊ ጌጤ እንዳሉት አሚኮ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ከ78ኛ ዓመቱ ጀምሮ እስከ 85ኛ ዓመቱ ድረስ የፈረሰኞች ማኅበርን በዓል በቀጥታ ስርጭት እና በዜና ሽፋን በነፃ በመስጠት ባሕሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ አስችሏል ነው ያሉት። ይህ አስተዋጽኦ የአገው ፈረሰኞች ማኅበርን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን ሚና እየተጫዎተ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
አሚኮ የብሔረሰቡን ባሕል፣ ቋንቋ እና ቱሪዝም በማስተዋወቅ የተወጣው ኀላፊነት ከፍ ያለ እንደኾነም ተናግረዋል። ባሕል እና ቋንቋውን በማስተዋወቅ በኩልም አሚኮ የአዊኛ ዝግጅት ክፍልን በመክፈት ማኅበረሰቡ በራሱ ቋንቋ ባሕሉን፣ ወጉን እና እሴቶቹን እንዲያስተዋውቅ ከፍተኛ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል። በተጨማሪም ያልታወቁ ባሕላዊ ቅርሶች እንዲጎለብቱ እና እንዲታወቁ ስለማድረጉም ጠቁመዋል። በተጨማሪም በአዊኛ ቋንቋ የሚዘፈኑ ዘፈኖች እንዲያድጉ እና የጃኖ ልብስም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ አሚኮ ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት።
አሚኮ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የቱሪስት መዳረሻዎች ከኾኑት ውስጥ እንደ ዘንገና ሐይቅ፣ ጥርባ ሐይቅ፣ ዶንዶር እና ቲስኪ ፏፏቴዎችን ለተመልካች በማሳየት እንዲተዋወቁ አድርጓል ብለዋል። የእጅ ጥበብ ውጤቶች እና የባሕላዊ ምግብ አሠራሮችን በማስተዋወቅ ምርቶቹ ከሀገር አልፈው በውጭ ገበያ እንዲታወቁ ጥረት ስለማድረጉም ጠቁመዋል።
አሚኮ እንደ መስቀል፣ አሱሪቴ፣ ገና እና ጥምቀት ያሉ የብሔረሰቡ ሃይማኖታዊ በዓላትን በቀጥታ ስርጭት በመሸፈን የአካባቢውን ባሕል እና ወጎች አስተዋውቋል። አቶ ወለሊ ጌጤ አሚኮ 30ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ጊዜ ጠንካራ ጎኖቹን በማስቀጠል ክፍተቶቹን ማስተካከል እንዳለበት ገልጸው ለመላው የአሚኮ ቤተሰብ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!