
ሁመራ፡ ነሀሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚዲያ መርህን ጠብቆ እየሠራ ያለ ሚዲያ መኾኑን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚኖሩ ምሁራን ገልጸዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር ዋና ሥራ አሥኪያጅ ገሠሠው ወንድም (ዶ.ር) አሚኮ ለዘመናት ተደብቆ የቆየውን የዞኑን ሕዝብ ባሕል፣ ወግ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አውጥቶ በማሳየት የአሚኮ ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
አሚኮ በዞኑ ሕዝብ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ የዘገባ ሽፋን በመስጠት ግንባር ቀደም ሚዲያ ነው ያሉት ምሁሩ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም የማይተካ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ቋንቋዎች ለሕዝብ ተደራሽ እየኾነ የመጣ ሚዲያ መኾኑንም ገልጸዋል። ይሄንን የሕዝብ ተደራሽነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የአካባቢው ሕዝብ ላለፉት ዘመናት በጭቆና ውስጥ የቆየው የሕዝቡ የአማራነት ዕውነት በአግባቡ ባለመውጣቱ ነው ያሉት ደግሞ እያቸው ተሻለ ናቸው።
ዕውነትን በማውጣት ረገድ የአሚኮ ሥራ ጉልህ ነው ብለዋል። አሚኮ በችግር ጊዜም ከማይካድራ እስከ ጭና የተፈጸመውን ግፍ ለዓለም ሕዝብ በማጋለጥ የሠራው ሥራ የሚረሳ አይደለም ነው ያሉት። በዚህም በአካባቢው አሚኮ ብቸኛ ሚዲያ መኾኑን ጠቁመዋል።
አሚኮ የሚዲያ ገለልተኝነትን እና መርህን ጠብቆ ሕዝብን እያገለገለ መኾኑንም አንስተዋል።
ይሄንን ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!