
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዝነኛው እና ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቶማስ ጃፈርሰን “ሚዲያ ከሌለው መንግሥት ይልቅ መንግሥት በሌለበት ሚዲያ እንዲኖር እመርጣለሁ” በሚለው አነጋጋሪ ሃሳባቸው በበርካቶች ዘንድ ይታወሳሉ፡፡
ፕሬዝዳንት ጃፈርሰን በአንድ ሀገር ውስጥ ከመንግሥት ይልቅ ሚዲያ እንዲኖር መምረጣቸው ሚዲያዎች የመንግሥትን ሚና ተክተው ይወጣሉ የሚል እምነት ኖሯቸው ሳይኾን ጠንካራ የሚዲያ ተቋማት ባሉበት ሀገር ውስጥ ጠንካራ መንግሥት መኖሩ አይቀሬ መኾኑን በመገንዘባቸው ነበር ይባልላቸዋል፡፡
በሌላ በኩል እውቁ የዲቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ ምሁር እና የኖቬል ሽልማት አሸናፊው አማንታ ያሲንም “ምርጥ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት ባሉበት ሀገር ውስጥ ርሃብ አይኖርም” ይላሉ፡፡ ምርጥ ጋዜጠኞችም ኾኑ ጠንካራ የሚዲያ ተቋማት ባሉበት ሀገር ውስጥ ርሃብ አይኖርም ሲባል ተቋማቱ መና ከሰማይ የሚያወርዱ ኾነው አይደለም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በአግባቡ በሚዲያ ተተችተው እና የጋራ መግባባት ተፈጥሮባቸው ሕዝብ እና መንግሥት በጋራ ይቆማሉ ከሚል እሳቤ እና ስሌት የመነጨ ነው እንጅ፡፡
ከአንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ በላይ ብዙም ባልተሻገረው የኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ ውስጥ አሚኮ ቀዳሚው ክልላዊ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ሁሉ አሚኮም ጅማሮው በሕትመት የሚዲያው ዘርፍ ነው፡፡ “በኩር” ጋዜጣም የአሚኮ የበኩር ልጅ ናት፡፡ ከትናንት እስከ ዛሬ በአሚኮ ቤት ነገን አሻግሮ መመልከትን እና መዳረሻን አውቆ መነሳትን የተቸራቸው የየዘመኑ የኮርፖሬሽኑ መሪዎች እና ሠራተኞች ያለፉባቸው የሕዝብ አገልጋይነት መንገዶች ጉልህ አሻራ አላቸው፡፡
አሚኮ ከ1987 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ላለፉት 30 ዓመታት የሰጠውን ሕዝባዊ ግልጋሎት በሚመጥ መልኩ “30 ዓመታትን በትጋት” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡ የአሚኮን ያለፉ ዓመታት አበርክቶ እና የቀጣይ ዘመን ተልዕኮዎችን አስመልክቶ ከኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ይርጋ ሲሳይ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
አቶ ይርጋ ሲሳይ አሚኮ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአማራን ሕዝብ ሥነ ልቦናዊ ከፍታ እና ልዕልና በሚመጥን መልኩ ለሕዝብ ጥቅም እና መብት መከበር ተግቷል ይላሉ፡፡ የክልሉ ሕዝብ የመልማት ፍላጎት ከመንግሥት ዐይን እና ጆሮ ውስጥ እንዲደርስ፤ የክልሉ ሕዝብ ነባር ባሕላዊ እሴቶች እና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በቀሪው ዓለም ሕዝብ ዘንድ በውል እንዲታወቁ እና የአማራ ሕዝብን ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት ፅኑ መሻትን በመግለጥ አበርክቶው የጎላ እንደነበር አንስተዋል።
አሚኮ የሕዝብን መብት እና ጥቅም የሚያስጠብቅ የሕዝብ ድምጽ ኾኗል ስንል መገለጫዎቹ ዘርፈ ብዙዎች ናቸው የሚሉት የቦርድ ሰብሳቢው ለዘገባዎቹ ቅድመ ጥናት የሚያደርግ፣ ከሕዝብ የሚነሳ፣ በሙያዊ መርህ የሚሠራ፣ አጀንዳ የሚሰጥ እና ችግር ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ቀድሞ በመገኘት ቀዳሚ እና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ መስጠት የኮርፖሬሽኑ መለያዎች ኾነዋል ነው ያሉት፡፡
በሥራዎቹም ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ እና በሕዝብ ልብ ውስጥ የማይጠፋ የሚዲያ ተቋም እየኾነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
አሚኮ ኢትዮጵያዊ ማንነትን እና ብሔራዊ አንድነትን ለማጉላት የሄደበት ርቀት የተፅዕኖ ደረጃውን የጎላ አድርጎታል ያሉት ሰብሳቢው በዚህ ተቋሙ ዕውቅና ብቻ ሳይኾን ዋጋም ከፍሏል ነው ያሉት፡፡ ጠንካራዋን ኢትዮጵያ ማየት በማይፈልጉ ኃይሎች ጥርስ ውስጥ የገባ ተቋም እንደነበርም አንስተዋል፡፡ ሙያዊ መርህ፣ በጋራ መቆም፣ ሕዝባዊ መሠረት እና በፈተናዎች መካከል አልፎ መሥራት መቻል ተቋሙ ሳይደበዝዝ እንዲቀጥል አድርጎታልም ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ሥነ ልቦናዊ ልዕልናው ከፍ ያለ፣ በወንድማማችነት እና እህትማማችነት የሚያምን፣ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር እና በጋራ በመቆም የሚያምን ሕዝብ ነው ያሉት ሰብሳቢው አሚኮ ለዚህ ትልቅ ሕዝብ የሚመጥን አበርክቶ እንዲኖረው ዛሬ እና ነገም ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ በትጋት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የአማራን ሕዝብ ትክክለኛ እና እውነተኛ ማንነት ለቀሪው ዓለም በትክክል ለመግለጥ “ከሀገር ባሻገር” ለመሥራት መዘጋጀት ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡ በሠራተኞቹ ትጋት፣ በመሪዎች ቁርጠኝነት እና ባለው ሕዝባዊ መሠረት አሚኮ የሚያልመውን ሁሉ እንደሚያሳካ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!