አሚኮን የማደምጠው በምክንያት ነው።

9

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ)

ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ ዘልቄያለሁ። የእውነት ለመናገር ይህ ቀዬ የሚናፈቅ አካባቢ ነው።

ከዚህ የሚናፈቅ ቀዬ ነዋሪ የኾኑትን አርሶ አደር ደረሰ አዱኛ አግኝቻቸዋለሁ። አርሶ አደር ደረሰ የዛሬን አያድርገውና በድህነት የሚኖሩ የዚያ የሚናፍቅ ቀዬ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ ስለነበሩበት ሁኔታ ሲናገሩ ዓመት ተለፍቶ የሚያገኙት ምርት ለቀለብ እንኳ ዓመት የማያደርስ ነበር ይላሉ።

ዛሬ ላይ የአርሶ አደር ደረሰ ታሪክ ተቀይሯል፤ ሀብታም ከሚባሉ አርሶ አደሮች ተርታ ተሰልፈዋል። አርሶ አደሩ ያችን የታሪካቸው ቀያሪ፣ የለውጣቸውን መዟሪያ ነጥብ ሲያስታውሱ አብሮ ከንግግራቸው የማይወጣው አሚኮ ነው። አሚኮ ባለውለታቸው እንደኾነ የሚናገሩት አርሶ አደሩ የለውጣቸው ጅማሮ መነሻ እንደኾነም ነግረውናል።

ዓመቱን ሲያስታውሱ ወደ 1997 አለያም 98 አካባቢ የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነው ይላሉ አንድ እርሳቸውን ሊለውጥ የሚችል የለውጥ ሃሳብ ሁሌም በሚከታተሏት ራዲዮናቸው የሰሙት።

በደሳሳ ጎጇቸው ከባለቤት እና ልጆቻቸው ጋር አመሻሽ አካባቢ ተቀምጠው እያወጉ ራዲዮኗም በጎን ታወራለች። በትክክል ማስታወሴን እርግጠኛ ባልኾንም የአርሶ አደሮች ጉዳይ የሚወራበት ውሎ በአርሶ አደሮች ቀዬ መርሐ ግብር ላይ የሚናገሩ አንድ አርሶ አደር ቀልባችንን ሳቡት ይላሉ።

አርሶ አደሩም ሲቀጥሉ የራዲዮኗ ሃሳብ የቤተሰቡን ቀልብ ስለገዛ ከቤተሰባዊ ወግ አቁመን ማዳመጥ ጀመርን ይላሉ። አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርን እና ማዳበሪያን በመጠቀማቸው መለወጣቸውን ብሎም የሚገርም ለውጥ ማምጣታቸውን ካዳመጥን በኋላ ለመተግበር ተነሳን ይላሉ።

መጀመሪያ አካባቢ እውነት መኾኑን ብንጠራጠርም ግን ደግሞ መሞከር እንዳለብን ወስነን ገባን ብለዋል።

ከዛም ራዲዮናችን ባስተማረችን አግባብ ተጠቅመን የሚገርም ለውጥ አመጣን የሚሉት አርሶ አደሩ በፊት ያገኙት ከነበረው 15 ኩንታል በሄክታር ወደ 40 ኩንታል ተሻገርን ይህም ድህነትን የተሰናበትንበት ትልቅ ምዕራፍ ነው ሲሉ አሚኮ የዋለላቸውን ውለታ አስታውሰው አሚኮን የሚያደምጡት በምክንያት መኾኑን ነገሩን።

አሁን ላይ በቀያቸው ሞዴል እና ሃብታም የሚባሉ ሰው መኾናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሩ አሚኮ ከዚህም በላይ እንዲሰፋ እና እንዲደረጅ እፈልጋለሁ ይላሉ። ለዚህም ከአሚኮ ሠራተኞች ባለፈ እኛ አርሶ አደሮች ባለቤት ነን ብለዋል።

አርሶ አደር ደረሰ አሚኮ ይበልጥ ተደራሽ ለመኾን መሥራት እንደሚጠበቅበት እና አሁን ላይ የሚታይበትን መቆራረጥ ቀርፎ የተሻለ ሚዲያ ኾኖ እንዲወጣ ፍላጎታቸው መኾኑንም ጠቁመዋል።

የአማራን ውበት፣ ማንነት፣ የተፈጥሮ ጸጋ፣ ማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ልህቀቱን ሊገልጥ የተመሠረተው አሚኮ የክልሉን ሕዝብ ከድህነት ማውጣትን ታሳቢ አድርጎ የተመሠረተ ሚዲያ ነው።

በአሚኮ የቴክኖሎጅ ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ ተሾመ ውዱ እንደነገሩን አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት ሕዝብ የሚቀይር ሥራ በመሥራቱ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተቀየረ እና የተለወጠ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደቻለም ነው የተናገሩት።

ሥራውን በበኩር ጋዜጣ ጀምሮ በቴክኖሎጅ እየላቀ የመጣው አሚኮ ከጋዜጣ በኋላ ሥራውን የጀመረው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአየር ሰዓት ኪራይ እንደነበር ተናግረዋል።

የአየር ሰዓቷ ትንሽ ብትኾንም እንኳን በወቅቱ አሚኮ የሕዝቡን የተደበቀ ጥበብ፣ ሃብት እና እሳቤ መግለጥ የቻለ የክልሉ ሕዝብ ሚዲያ መኾን እንደቻለም ተናግረዋል። ይህ ሥራም ክልሉን በመላው ሀገሪቱ ብሎም በዓለም እንዲታወቅ ትልቅ በርን ከፍቷል ይላሉ ምክትል ሥራ አሥፈጻሚው።

30 ዓመታት በትጋት የሠራው አሚኮ ከኪራይ ሥራ ወጥቶ ራሱን እንዲችል ብዙ ጥረት ተደርጎ መሳካቱንም ነው የጠቆሙት።

አሁን ላይ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጅዎች ሁሉ ታጥቆ ሙሉ የአየር ሰዓትን በራሱ አቅም መሥራት የቻለበት ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል። ተቋሙ ከነበረበት የአናሎግ ሥርጭት ወደ ዲጂታል ሥርጭት ተሻግሮ አሁን ላይ የራሱ ቀለም ያላቸው ዝግጅቶችን ለማኅበረሰቡ እያደረሰ ነው ብለዋል።

ከራዲዮ ሥርጭት አኳያ በመካከለኛ ሞገድ የተወሰኑ አካባቢዎችን እንደሚደርሱ እና በኤፍ ኤም በስድስት ጣቢያዎች ለመድረስ ተቋሙ የሠራ ሲኾን እነዚህ ተደራሽ የማይኾኑባቸው አካባቢዎች ላይ በተለይም ስምንት ቦታዎች ላይ ደግሞ ጋፕ ፊለር በመጠቀም ተደራሽ ለማድረግ መሞከሩንም ነው የገለጹት።

ይህ ማለት ግን ክልሉን መቶ በመቶ ሸፍኖል ማለት ባይቻልም በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ ግን ተደራሽ ለመኾን መሠራቱን አስገንዝበዋል።

ከቴሌቪዥንም አኳያ በቋሚነት ስርጭት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ በየጊዜው የአየር ሰዓቱን እያሳደገ እስከ 24 ሰዓት ሥርጭት መድረሱን አመላክተዋል።

አሚኮ ሕዝብን ለመለወጥ ታሳቢ ያደረገ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲኖረው ለማድረግ መሠራቱን የጠቆሙት አቶ ተሾመ አሁን ላይ ሙሉ ባለ ኤች ዲ ጣቢያ ለመኾን የበቃ ትልቅ ተቋም እንደኾነም አስገንዝበዋል።

ከቀረጻ አኳያም አሚኮ ከጊዜ ጊዜ እያደገ የሄደ እና ዘመኑ ባፈራው የመሥክ ሥራ በሚከናወንበት ኦቪቫን መሥሪያ ከፍ ያሉ ሥራዎችን ለሕዝብ ተደራሽ እያደረገ ያለ ተቋም መኾኑንም ጠቁመዋል። ምንም እንኳን በሚፈጠር የቴክኒካል ችግር መቆራረጦች ከመኖራቸው በተጨማሪ ተደራሽ መኾን ባለባቸው አካባቢዎች የክልሉ 25 ዓመታትን ስትራቴጅክ ፕላን በመከተል ለለውጥ የሚተጋ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ጥረት እንደሚደረግም ነው ያብራሩት።

በተለይም በቀጣይ አሚኮ ያሉትን ሃብቶች በመጠቀም እና በማዘመን የሕዝብ የለውጥ ምክንያት ኾኖ ለመውጣት የሚሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ቴክኖሎጅ ተለዋዋጭ ቢኾንም አሁን ባለው ሁኔታ ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጅዎች አሚኮ እንዳለው እና ሕዝብን ለመቀየር እየተጠቀመባቸው ስለመኾኑም አብራርተዋል።

አሚኮ ከምንም በላይ ሃብቱ የሰው ኃይሉ ነው ያሉት አቶ ተሾመ ይህን ኃይል የልማቱ ዋና አንቀሳቃሽ ለማድረግ በአጭር እና በረጅም ጊዜ እቅድ እስከ ውጭ ድረስ ትምህርት እና ተሞክሮ በማለዋወጥ ሀገርም ይሁን ክልሉ የሚኮራባቸው ብቁ ባለሙያዎች ማፍራት የቻለ ተቋም ነው ብለዋል።

በተለይም የውስጥ አቅሙን ተጠቅሞ እርስ በእርስ የሚያደርገው መማማር ለለውጡ ምክንያት ተደርጎ እንደሚወሰድም ነው ያስገነዘቡት።

በቀጣይ ተቋሙ ያልደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች እየተከታተለ በመሥራት የተሻለ በዕውቀት ተመሥርቶ ልማቱን የሚያሳልጥ ተቋም ለመገንባት ጥረት እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥራት ያለው የመማር ማስተማር ሥርዓት ለመዘርጋት ሁሉም በጋራ ሊሠራ ይገባል።
Next articleየአርሶ አደሮችን ሕይወት እየቀየረ ያለው የፍራፍሬ ምርት፦