
ጥራት ያለው የመማር ማስተማር ሥርዓት ለመዘርጋት ሁሉም በጋራ ሊሠራ ይገባል።
ገንዳ ውኃ: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የመተማ ወረዳ ተወካይ አሥተዳዳሪ እና የግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት ፍቃድ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የትምህርት ሥርዓቱን ከአሁኑ ማስጀመር እና በጥራት ማከናወን ይገባል ብለዋል።
ዛሬ ትምህርት ላይ ጠንክሮ ከተሠራ ነገ የተሻለች ሀገር መገንባት ይቻላል ያሉት ተወካይ አሥተዳዳሪው ለዚህ ደግሞ ትውልዱን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ጥራት ባለው የማስተማር ዘዴ ማስተማር የሁሉም ድርሻ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት የትምህርት ሥርዓቱን ለማስኬድ ጸጥታው ማነቆ ኾኖ ቢቆይም ችግሩን ተቋቁመው የመማር ማስተማሩን ሥራ እንዳከናወኑ የመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በየነ አዳነ ተናግረዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም ከባለፈው ዓመት በተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት እንደሚሰጥም ኀላፊው አመላክተዋል።
በትምህርት ዘመኑም የተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምር እና የግብዓት አቅርቦት እንዲሟላ በትጋት እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተማሪዎችን ቀስቅሶ ወደ ትምህርት እንዲመጡ የማድረግ ኀላፊነት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ መምህር የኛነው መንግሥቴ ከመደበኛው የመማር ማስተማር ውጭ ተማሪዎችን በማገዝ የተለያዩ ወርክ ሽቶችን በማዘጋጀት ለፈተና ብቁ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
ቀጣይም ተማሪዎችን በመቀስቀስ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመጡ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት።
ሌላኛዋ ተሳታፊ መምህር ማስተዋል ያለው ተማሪዎችን ከመደበኛው የትምህርት ክፍለጊዜ በተጨማሪ በማስተማር ለጥሩ ውጤት እንዲበቁ ጥረት እንዳደረጉ አስረድተዋል።
ለሴት ተማሪዎችም ልዩ ድጋፍ በማድረግ በትምህርታቸው ጠንካራ እንዲኾኑ ስለመሥራታቸውም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!