
የማኅበረሰቡን እሴት አደጋ ላይ የሚጥሉ የቁማር ተግባራትን ማስቆም ይገባል።
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበረሰቡን እሴት አደጋ ላይ የሚጥሉ የቁማር ተግባራትን ለማስቆም እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ደንብ ማስከበር እና መከላከል ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ቁማር በትውልድ ላይ የሚያሳርፈው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ በመኾኑ ለማኅበራዊ ቀውስ በመዳረግ ሱስ እስከመኾን የሚደርስ ሕገ ወጥ ተግባር ነው።
በሕግ ከተፈቀደላቸው ሎተሪዎች እና ውርርዶች ውጭ የሚደረጉ የቁማር ተግባራት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 789 ንዑስ አንቀጽ አንድ መሠረት ሕጋዊ እርምጃዎች የሚያስወስዱ ናቸው።
በዚህ ረገድ በከተሞች አካባቢ በስፋት የሚስተዋለው ቁማር ጥብቅ የኾነ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ ካልተከናወነ ትውልድ ላይ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ የከፋ እንደሚኾን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሃብት እና ንብረታቸውን በማስያዝ የቁማር ጨዋታ የተጫወቱ ሰዎች ለከፋ ቀውስ መዳረጋቸውን ጭምር ነዋሪዎቹ አንስተዋል ፡፡
ለማኅረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ተግባራትን ከመስጠት ጎን ለጎን ሕጋዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መኾኑን የእቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር እና መከላከል ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቴዎድሮስ አየለ ገልጸዋል፡፡
ከተማ አሥተዳደሩ የተከለከሉ የቁማር ተግባራትን ለማስቆም ተከታታይ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ደንብ ማስከበር እና መከላከል ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ነብዩ አሰፋ ናቸው፡፡
በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት በከተማው በሚገኙ 60 የቁማር ቤቶች ላይ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል። ተግባሩን ለመከላከል ማኅበረሰቡም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የማኅበረሰቡን እሴት አደጋ ላይ የሚጥሉ የቁማር ተግባራትን ለማስቆም ቀጣይነት ያላቸው ሕጋዊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ነው ያሉት አቶ ነብዩ፡፡
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!