
“የአሚኮ 30ኛ ዓመት ሲከበር የኔም ልደት እንደኾነ ይሰማኛል” ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት መንግሥቴ
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ለሁሉ አቀፍ ዕድገት እና ልማት የአጋዥነት ሚናው ከፍተኛ ነው።
የአሁኑ አሚኮ የበፊቱ የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ክልላዊ የብዙኀን መገናኛ አውታር ኾኖ ሲቋቋም ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ቀዳሚው እንደኾነ ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ የብዙኀን መገናኛ ዕድገት በኢትዮጵያ ከተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ከትበዋል።
የአማራ ድምጽ የአሁኑ አማራ ሬዲዮ የሙከራ ጊዜውን ካጠናቀቀ በኋላ ቅዳሜ ግንቦት 16/1989 ዓ.ም ተመርቆ መደበኛ የሥርጭት መርሐ ግብሩን ሲጀምር በክልሎች ደረጃ የመጀመሪያው የመካከለኛ ሞገድ ሬዲዮ ጣቢያ መኾን እንደቻለም ጋዜጠኛ መዝሙር መዝግበዋል።
ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት መንግሥቴ ከሐምሌ 1989 ዓ.ም ጀምሮ በጣቢያው ውስጥ ከሪፖርተርነት እስከ ኀላፊነት ቦታ ሠርታለች።
እኔ ሥራ የጀመርኩት ለአማራ ሬዲዮ የዜና አንባቢነት ሙያ በነጻ ነው የምትለው ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት የአሚኮ 30ኛ ዓመት ዕድሜ የሚቆጠረው በኩር ጋዜጣ ከጀመረችበት 1987 ዓ.ም ጀምሮ ነው ትላለች።
በቆይታየ ከጀማሪ ሪፖርተርነት አንስቶ አሁን ካለሁበት የአሚኮ አዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ምክትል ዳይሬክተር ድረስ የኖርኩበት ቤቴ ነው ብላለች። የሬዲዮ ሂደት መሪ፣ ምክትል አዘጋጅ፣ ዋና አዘጋጅ እና ሌሎች ኀላፊነቶች ላይ በፍቅር እንደሠራች ታስታውሳለች።
ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ለ28 ዓመታት ያክል የቆየሁበት አሚኮ ለኔ በኩራት የምናገርለት ቤቴ ነው ትላለች። “የአሚኮ 30ኛ ዓመት ሲከበር የኔም ልደት እንደኾነ ይሰማኛል” ነው ያለችው።
የሬዲዮ ዘርፍ በተለይ ለታችኛው ማኅበረሰብ ትልቅ ባለውለታ ነው። የአማራ ሬዲዮ በኢትዮጵያ ካሉ ክልሎች ቀዳሚው የመረጃ እንደኾነም ተናግራለች።
የያኔው የአማራ ድምጽ የአሁኑ አማራ ሬዲዮ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጥቂት የአየር ሰዓት በመውሰድ ይሠራ እንደነበር ታስታውሳለች። ይሁን እና ትላለች ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት በዚያች የአጭር ሰዓት ሥርጭት የሚተላለፉ መልዕክቶች ቁምነገር ያዘሉ እና አይረሴ ነበሩ ብላለች። ለገጠሩ ማኅበረሰብ ይተላለፉ የነበሩ ዝግጅቶች የብዙዎችን ሕይወት የቀየሩ ነበሩ።
በዕለቱ የነበረው የተደራሽነት መጠን ከክልሉ አልፎ ሌሎች አካባቢዎችም ይከታተሉት እንደነበር ነው የተናገረችው። አርሶ አደሮች ከደቡብ ክልል ሳይቀር በአማራ ሬዲዮ እየደወሉ አስተያየት ይሰጡን ነበር ነው ያለችው። በግብርና ሕይወታቸው ላይም አቅም እንደኾናቸው ይነግሩን ነበር ብላለች።
እናም ያኔ በትንሽ የሰው ኀይል ብዙ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ተግባራት ይሠሩ እንደነበር ትናንቷን ነግራናለች።በውስን የሰው ኀይል እና በውስን የሥርጭት መሣሪያዎች ሥራውን የጀመረው አሚኮ አሁን የቴክኖሎጅ ባለቤት መኾኑ እንደሚያስደስታትም ገልጻለች።
የተቋሙ ሠራተኞችም ተባባሪ እና ቅን እንደነበሩ አስታውሳለች። የራዲዮ ጋዜጠኝነት በፍቅር የሚሠራ እና ለገጠሩ ማኅበረሰብ ተደራሽ መኾን የቻለ የተከበረ ሙያ ነው ብላለች።
ሥራውን እየከወነ ዛፉ ሥር ላይ ሬዲዮኑን አስቀምጦ ለሚሠራው አርሶ አደር ልዩ ትርጉም የሚሰጥ ዘርፍ እንደኾነ ነው የገለጸችው። ሬዲዮ ዕውነትን የሚያካፍል ጓደኛ ነው ትላለች ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት። ሬዲዮ በማዳመጥ ሕይወታቸውን ያስተካከሉ አድማጮች ነበሩ ነው ያለችው።
እንደ አሁኑ ዘመን ማኅበራዊ ሚዲያው ባልተስፋፋበት ሬዲዮ ትልቅ ባለውለታ እንደነበር ነው የገለጸችው። በማኅበራዊ ሚዲያ ያልታጠረው የሬዲዮ ተጽዕኖ ፈጣሪነት በዚያ ዘመን ከፍተኛ እንደነበርም ተናግራለች። ቤቱ ላይ ሬዲዮ ያለው ሰው በራሱ ክብር እና ዝናም ነበረው ትላለች የሬዲዮን ባለውለታነት ስታስታውስ።
የአሚኮ የሬዲዮ ዘርፍ ከተቋቋመለት ዓላማ አንጻር አበርክቶው ጉልህ እንደኾነ የምትናገረው ጋዜጠኛዋ አማራ ሬዲዮም ኾነ ሌሎች የአሚኮ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች ማኅበረሰቡን በማንቃት እና መረጃን በማድረስ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዘመን አይሽሬ ነው ብላለች።
አሚኮ የሬዲዮ ዘርፍ የማኅበረሰቡ የዕውነት ማረጋገጫ ኾኖ ቆይቷል ነው ያለችው። ሰዎች ማን አለ? የሚለውን መረጃ ለማረጋገጥ አማራ ሬዲዮ ብሏል ከተባለ ዕውነት ነው ተብሎ ይታመናል። አማራ ሬዲዮ ካለማ ልክ ነው ይባላል ብላለች።
አሚኮ የሬዲዮ ዘርፍ በልማት፣ በማኅበራዊ ጉዳይ፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው ዘርፍ አሻራው ቀላል እንዳልኾነ ነው የገለጸችው። በ1989 ግንቦት ወር የጀመረው የአማራ ሬዲዮ ያመጣው የተፈላጊነት መጨመር ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9 የከተማውን ማኅበረሰብ ታሳቢ በማድረግ በ1994 ዓ.ም እንዲከፈት በር ኾኗል።
የኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9 በከተማው አካባቢ ሥርጭት መጀመሩ ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ልምምዱን ያመቻቸ ነበር ብላለች ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት መንግሥቴ። ሰዎች የሌሎችን ሃሳብ የመቀበል ዝንባሌያቸው እንዲዳብርም የኤፍ ኤም ጣቢያዎቻችን አበርክቶ ትልቅ ነው ብላለች። ጣቢያዎቹ ማኅበረሰቡ በቀጥታ እየገባ ሃሳብ የሚለዋወጡበትን መንገድ ያሳዩ ናቸው ነው ያለችው።
ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9 ሥርጭቱን ሲጀምር ጤና ይስጥልኝ ብየ የጀመርኩት እኔ ነበርኩ የምትለው ጋዜጠኛዋ የኾነው ግን ባጋጣሚ እንጅ ታስቦበት የተመደብኩ አልነበረም ነው ያለችው። አጋጣሚው ግን የሕይወቴ አንዱ ክፍል በመኾኑ እድለኛ ነኝ ብላለች።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከትናንት እስከ ዛሬ ዕድገቱ የማያቋርጥ ነው። ሠራተኞቹ ለሚዲያው ሞተር ናቸው ነው ያለችው። የታጠቀው ዘመናዊ የሚዲያ መሣሪያም ከትናንቱ አንጻር ከፍ ያለ ነው ብላለች።
አሁን ላይ ሌሎች ትልልቅ ሚዲያዎች የሌላቸው ሃብት በአሚኮ ቤት መገኘቱ ሌላው የግዝፈቱ ማሳያ እንደኾነም ገልጻለች። ከማሰራጫ ጣቢያ እስከ ተደራሽነት ስፋት ድረስ የሀገር ኩራት ተቋም ነው ብላለች። እዚህ በመድረሱም በተለያዩ ባለሥልጣናት ዕውቅና እየተቸረው ያለ ተቋም እንደኾነም ነው የተናገረችው።
በቀጣይም አሚኮ በሀገር አቀፍ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የመኾን ሕልሙን ይዞ እንዲጓዝ እፈልጋለሁ ብላለች። “ጋዜጠኝነት ደመወዝ የሚበላበት ሙያ ሳይኾን ማንነትን አሳልፎ ለማኅበረሰቡ የሚሰጥበት የተከበረ ሙያ እንደኾነ ነው” የተናገረችው። እኛም የአሚኮ ቤተሰቦች ጥሩ ሥራ ሠርተን ስሙን የበለጠ የምናስጠራ ኾነን መገኘት አለብን ነው ያለችው።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!