
“አሚኮ የኀብረተሰብ ትምህርት ቤት ነው”
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት የዛሬው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በ1987 ዓ.ም በበኩር ጋዜጣ አማካኝነት መረጃን ለኀብረተሰቡ በማድረስ የማስተማር፣ የማሳወቅ፣ እና የማዝናናት ተግባሩን ጀምሯል።
በሂደትም በቴሌቪዥን፣ በመደበኛው ሬዲዮ፣ በኤፍ. ኤም፣ በብሔረሰብ ጋዜጦች እና በዲጂታል ሚዲያ አማካኝነት አድማሱን እያሰፋ እነኾ 30 ዓመታትን ደፈነ።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የአሚኮ የሥራ ውጤት እንዴት ይገለጽ ይኾን?
“ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” እንዲሉ አበው ባለፉት 33 ዓመታት በጋዜጠኛነት እያገለገለ የሚገኘው ታምራት ሲሳይ አሚኮ ብዝኀ ልሳን በመኾን ኀብረተሰቡን እያስተማረ እና እያነቃ ይገኛል ባይ ነው።
ጋዜጠኛ ታምራት አክሎም ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ማድረጉ የአሚኮ ሌላው የጥንካሬ መገለጫ ነው ሲል ዋቢ አስቀምጧል።
አሚኮ ውግንናው ለሕዝብ እና ለሕገ መንግሥቱ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ታምራት በሀገሪቱ በየትኛውም አቅጣጫ የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎች ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን በውል ተገንዝበው በአግባቡ እንዲገለገሉበት አሚኮ እየሠራ መኾኑን አንስቷል።
ኀብረተሰቡ አመክንዮ ላይ ተመርኩዞ መብቱን ጠያቂ እና ግዴታውን አክባሪ ሞጋች እንዲኾን አሚኮ ለመሥራቱ “የከተሞች መድረክ” ይሰኝ የነበረውን የሕዝብ ድምጽ በአስረጅነት ጠቅሷል።
በአማራ ክልል ለሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች በቋንቋቸው አማካኝነት ሚዲያው ተደራሽ መኾኑ ኀብረ ብሔራዊነቱን አስመስክሯል የሚለው ጋዜጠኛ ታምራት ለባሕል፣ ወግ፣ እሴት እና ትውፊት ማደግ እና መዘመን አሚኮ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።
የኪነ ጥበብ፣ የበጎ አድራጎት እና የሀገርህን ዕወቅ ክበባት በየአካባቢው ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲስፋፉ እና በተለይ ወጣቶችን መሪ ተዋናይ በማድረግ ኀብረተሰቡ ከትሩፋታቸው ተቋዳሽ እንዲኾኑ አሚኮ ሠርቷል ባይ ነው።
ማኀበረሰቡ ኪነ ጥበብን ለልማት፣ ለባሕል ግንባታ፣ ለመጤ ልምድ መግሪያ እና መከላከያ እንዲገለገልበት የአሚኮ አበርክቶ ከፍተኛ እንደኾነ ጋዜጠኛ ታምራት ተናግሯል። በተለይ ደግሞ ወጣቱ ወደ ውጭ እንዳያማትር፣ በራሱ ባሕል እንዲያጌጥ አሚኮ እያስተማረ ይገኛል ብሏል።
ባሕላዊ በዓላት በአግባቡ እንዲከወኑ በማድረግ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር ረገድ አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። (እነ ሶለል፣ ቡሄ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ እንግጫ ነቀላ…) በመጥቀስ። በመኾኑም የባሕል አምባሳደር፣ የሰላም ዘማሪ እና ጠበቃ ኾኖ ዘልቋልም ነው ያለው።
በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ ፣ ባሕላዊ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ቅርሶችን፣ የመስህብ ሥፍራዎችን ለዓለም ማኀበረሰብ አስተዋውቋል፤ እንዲሁም ሃብቶቹ ይዘታቸውን ሳይለቁ እንዲለሙ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል ነው ያለው።
እንደ ሀገር ድንበር ሲወረር ሕዝብ “ሆ !” ብሎ እንዲወጣ እና የሀገሩን ልዑላዊነት በደም እና አጥንቱ እንዲጠብቅ አሚኮ ያደረገው የመቀስቀስ፣ የማንቃት እና የማስተማር ተግባር ከፍተኛ ነው።
አሚኮ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ አደጋዎች ሲከሰቱም ከፊት ኾኖ ሕዝብ በማንቃት እና በማስተማር ሀገራዊ ግዴታውን ለመወጣቱ በአስረጅነት ለኮሮና ቫይረስ ግንዛቤ የተደረገውን ርብርብ ጠቅሷል።
የስፖርት ማዘውተሪዎች እንዲለሙ እና ስፖርት ከመዝናኛነቱ ባሻገር ፋይዳው የጎላ መኾኑን አሚኮ ለማሳየቱ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን በማሳያነት ጋዜጠኛ ታምራት ጠቅሷል።
በጠቅላላው አሚኮ በበጎው ኀብረተሰብ ለውጥ አይነተ ብዙ እና ብዝኀ ልሳን ኾኖ በማስተማር አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገቡን ጋዜጠኛው ተናግሯል።
ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያውያን እና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለእንግሊዝኛ እና አረበኛ ቋንቋ ታዳሚያን ጭምር ተአማኒ መረጃ በመስጠት ሰው ተኮርነቱን አስመስክሯል፤ እያስመሰከረም ይገኛል ነው ያለው።
ሌላው አስተያየት ሰጭ ጋዜጠኛ ጣሰው መንግሥቴ በመምህርነት እና በጋዜጠኝነት ከ41 ዓመታት በላይ አገልግሎ በቅርቡ ከአሚኮ ጡረታ ወጥቷል።
ጋዜጠኛ ጣሰው አሚኮን የኀብረተሰብ መማማሪያ ትምህርት ቤት ነው ሲል ገልጾታል። አሚኮ “ለኀብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!” የሚለውን መለያ መሪ ቃሉን ከሕዝብ ጎን በመቆም የሕዝብ ችግር መፍትሔ እንዲፈለግለት፣ ጥሩው ነገር ደግሞ ይበልጥ እንዲጠናከር በከተሞች መድረክ አስመስክሯል ሲል አወድሶታል።
አሚኮ ኀብረተሰብን ከማስተማር ባለፈም በርካታ ጋዜጠኞችን እያሠለጠነ፣ በሙያ እና ሥነ ምግባር እያነጸ ለሌሎች ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጋዜጠኛ ጣሰው ተናግሯል።
“እኔን አሚኮ ብቁ ጋዜጠኛ አድርጎ ሠርቶኛል። በውስጡ እያለሁ በየዕለቱ በሚደረገው የእርስ በእርስ መማማርም ዕውቀት ገብይቻለሁ፤ በማኀበራዊ ሕይዎቴም ትልቅ ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል፤ በቃ! አሚኮ ኀብረተሰብን በዘርፈ ብዙ ዕውቀት እና ስብዕና አንጾ የሚያወጣ ትምህርት ቤት ኾኖ አግኝቼዋለሁ” ሲል ገልጿል።
በበኩር ጋዜጣ መረጃን ለኀብረተሰብ በማድረስ የጀመረው አሚኮ በ30 ዓመታት ጉዞው የሁለት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ የአራት ጋዜጦች፣ የሰባት ሬዲዮ ጣቢያዎች እና ሁሉንም አማራጮች የያዘ የዲጂታል ሚዲያ ባለቤትም የኾነ ግዙፍ ተቋም ነው።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!