አሚኮ በ30 ዓመታት ጉዞው ለአካል ጉዳተኞች ድምጽ መኾን ችሏል።

20

አሚኮ በ30 ዓመታት ጉዞው ለአካል ጉዳተኞች ድምጽ መኾን ችሏል።

ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት ጉዞው አካል ጉዳተኞች የሚገባቸውን ግልጋሎት እንዲያገኙ እና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ሢሠራ ቆይቷል።

አሚኮ በጉዞው ውስጥ ከአካል ጉዳተኞች ጋር የነበረውን ቁርኝት የነገሩን የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የቦርድ አባል ባንችዓምላክ አቤ አሚኮ አካል ጉዳተኞችን ከማካተት አንጻር ከትናንት ዛሬ የተሻለ ሥራ እየሠራ ነው ይላሉ።

ከዚህ በፊት በሁሉም ሚዲያ ስለ አካል ጉዳተኞች የሚሠራ ዘገባ ጥቂት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን በዜና ዘገባዎቹም ኾነ በአንዳንድ ፕሮግሞች ላይ የአካል ጉዳተኞችን ተግባር እንደ ሌሎች ሽፋን እየተሰጠው ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

አሚኮ እንደ ክልል በሚሠሩ ሥራዎች መስማት ለተሳናቸው አካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲኾን የምልክት ቋንቋ ባለሙያ በመቅጠር እና በፕሮግራሙ ላይ በማካተት የሚሠራው ሥራ ለሌሎች የሚዲያ ተቋማት ምሳሌ የሚኾን እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡

በራዲዮም ንጋት ፕሮግራም በሚል ለሌሎች አስተማሪ ሊኾኑ የሚችሉ አካል ጉዳተኞችን በመጋበዝ ለኅብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ሠርቷል ብለዋል፡፡

“በቀጣይ ለአካል ጉዳተኞች እኛ እንችላለን የሚለውን የምናሳይበት፣ ለሰፊው የማኅበረሰብ ክፍል ስለ አካል ጉዳተኞች ግንዛቤ የምንፈጥርበት እና የተለያየ ፕሮግራም የምንሠራበት የአየር ሰዓት እንዲሰጠን ምቹ ሁኔታዎች ቢፈጠር መልካም ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሚኮ በኢትዮጵያ ካሉ ቀደምት ሚዲያዎች ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ድምጽ የሚሰማበት ሚዲያ ነው ያሉት የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ ናቸው፡፡

ፕሬዝዳንቱ በተለይ እንደ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ብዙ ሥራዎች የሠራንበት፣ እራሳችንን ያስተዋወቅንበት፣ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ግንዛቤ የፈጠርንበት፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ የወጡ የሕግ ድንጋጌዎችን ያስተዋወቅንበት፣ የአካል ጉዳተኛ ችግሮችን ለማኅበረሰቡ እንዲደርሱ ያስተዋወቅንበት ሚዲያ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በክልሉ አካል ጉዳተኞች ስም ለአሚኮ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ቀደም ሲል አሚኮ እንደሌሎቹ ሚዲያዎች አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ ሥራ ላይ ውስንነት ይታይበት እንደነበር የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዕቅዱ አንድ አካል በማድረግ እኛም ሃሳብ እንድናዋጣ እና ሥራዎቻችን እንድናስተዋውቅ በማድረግ ብዙ ሥራ ሠርቷል” ነው ያሉት፡፡

በተለይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ ዘርፉ አርዓያ የኾኑ አካል ጉዳተኞችን በማስተዋወቅ ሌሎች እንዲማሩባቸው የማድረግ ሥራ በመሥራት እና አካል ጉዳተኞችን የማነቃቃት እና ይቻላል የሚለውን መንፈስ እንዲያሳድሩ በማድረግ በኩል የነበረው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው ተቋሙ እስካሁን የሠራቸውን ሥራዎች እና ሚዲያው ምን ይመስላል የሚለውን ሲያስቃኝ እኛም እንድንጎበኝ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

“ጉብኝቱ አሚኮ ለአካል ጉዳተኞች ምን ምቹ ሁኔታወችን ፈጥሯል የሚለውን እንድንገነዘብ አድርጓልም” ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ ሚዲያው ለአካል ጉዳተኞች ያለውን ቅርበት ያሳየ ነው፡፡ እኛም ቤተኛ እንድንኾን ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮልናል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ የአካል ጉዳተኞች የግንዛቤ ፈጠራ ዘርፍ ገና ጅምር በመኾኑ ከዚህ በበለጠ እንዲሠራላቸውም ጠይቀዋል፡፡

የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሌሎች ትኩረት የሚሹ ወገኖች ላይ መሥራት የተቋሙ ግዴታ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡ አሚኮ በተለያዩ ቋንቋዎች ሁሉንም ያማከለ መረጃ ወቅቱን ጠብቆ እያደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ሥራዎችን መሥራት የተቋሙ አንዱ አካል በመኾኑ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በምልክት ቋንቋ መረጃዎችን ሲያደርስ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ዋና ሥራ አሥፈጻሚው በቀጣይ ጊዜያት ተቋሙ በሚያከናውናቸው ሁሉን አቀፍ የዘገባ ሥራዎችም ላይ አካል ጉዳተኞችን አካትቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ500 በላይ የሚኾኑ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል።
Next article“አሚኮ የኀብረተሰብ ትምህርት ቤት ነው”