በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ500 በላይ የሚኾኑ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል።

45

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ500 በላይ የሚኾኑ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል።

እንጅባራ: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም ለማጽናት የተከናወኑ ተግባራት እና የተገኙ ስኬቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ቢሻው ለሁለት ዓመታት ገደማ የዘለቀው የፀጥታ ችግር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል ኅብረተሰቡን ለተራዘመ ስቃይ ዳርጎ መቆየቱን ተናግረዋል።

በአሁ ወቅት የፀጥታ መዋቅሩ ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር በመቀናጀት በሠራቸው ተግባራት አብዛኛው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ነው ያሉት።

የሰላም መደፍረስን ተገን አድርገው በተወሰኑ አከባቢዎች የሚስተዋሉ ዘረፋ፣ እገታ እና መሰል ወንጀሎች እየቀነሱ መምጣታቸውንም ኀላፊው አንስተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ500 በላይ የሚኾኑ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከኅብረተሰቡ ጋር መቀላቀላቸውን ነው ኀላፊው ያነሱት። ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

አንጻራዊ ሰላም ያለባቸውን ቀጣናዎች ወደ ተሟላ ሰላም ለማሸጋገር የሚያስችሉ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነም አንስተዋል።

የታጠቁ ኃይሎች ለሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጡ እና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ መደበኛ ሕይዎታቸው እንዲመለሱም መምሪያ ኀላፊው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በርካታ ሠራተኞችን ይዞ ወደ አንድ ግብ እና ዓላማ መምጣት በቀላሉ የሚገኝ ውጤት አይደለም” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleአሚኮ በ30 ዓመታት ጉዞው ለአካል ጉዳተኞች ድምጽ መኾን ችሏል።