
“በርካታ ሠራተኞችን ይዞ ወደ አንድ ግብ እና ዓላማ መምጣት በቀላሉ የሚገኝ ውጤት አይደለም” አቶ ይርጋ ሲሳይ
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አጀማመሩ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ለደረሰበት ከፍታ ፍንጭ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ተፈጥሯዊ ዕድገቱ እና ፍጥነቱ ግን ገና ብዙ እንደሚጓዝ አብሪ ምልክቶቹ ኾነዋል፡፡ አሚኮ በየጊዜው አዳጊ፤ የአሚኮ ቤተሰቦችም የምንጊዜም ተማሪዎች ናቸው፡፡ አሚኮ እና የአሚኮ ቤተሰቦች ውጣ ውረድ የሚያበረታቸው እንጅ የማይበረታባቸው፣ ፈተና የሚያሠለጥናቸው እንጅ የማይሰለጥንባቸው የሙያ ተማሪ እና ትምህርት ቤት ኾነው 30 ዓመታትን በትጋት ዘልቀዋል፡፡
በትንሽ ሠራተኞች እና በአንድ የሕትመት ዘርፍ የዛሬ 30 ዓመታት እንደ ተቋም አንድ ብሎ ሥራ የጀመረው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ዛሬ በመላው ዓለም መደመጥ የሚችል እና ብዝኀነት መለያው የኾነ የሚዲያ ተቋም ለመኾን በቅቷል፡፡
አሚኮ አሁን ላይ ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ፣ ሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎች፣ ሰባት የኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያዎች፣ አንድ መካከለኛ ሞገድ ራዲዮ፣ በርካታ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች፣ ዘርፈ ብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች፣ 12 ቋንቋዎች እና ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ባለቤት ነው፡፡
የሕዝባዊ መሠረት እና ሙያዊ እሴት ባለቤት የኾነው አሚኮ ያለፈባቸውን ሦስት አስርት ዓመታት ጉዞ “30 ዓመታትን በትጋት” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበረ ይገኛል፡፡
የአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ ይርጋ ሲሳይ የኮርፖሬሽኑን የ30 ዓመታት ክብረ በዓል አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አሚኮ በተቋም ግንባታ ሥራዎቹ ምሳሌ መኾን የሚችል ተቋም ኾኗል ይላሉ፡፡ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ለለውጥ ሥራዎች በሚመች መልኩ ሳይንሳዊ እና ሙያዊ ኾኖ ተዋቅሯል ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው ይህም እንደ ክልል ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገርም ትምህርት የሚወሰድበት ተቋም እንዲኾን አስችሎታል ነው ያሉት፡፡
ሃብትን በውጤታማነት መጠቀም የአሚኮ መለያ ኾኗል ያሉት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው ዘመኑ ያፈራቸውን ታላላቅ የሚዲያ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ለመጠቀም የሄደበት ርቀትም አስተማሪ ነው ይላሉ፡፡ የሙያተኞቹን ዕውቀት እና ክህሎት በሥራ ላይ ልምምድ፣ በሥልጠና እና በልምድ እያዳበረ የመጣበት መንገድም በተቋም ግንባታ ሂደቱ አስተማሪ እንደኾነ አንስተዋል፡፡
“በርካታ ሠራተኞችን ይዞ ወደ አንድ ግብ እና ዓላማ መምጣት በቀላሉ የሚገኝ ውጤት አይደለም” ያሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ አሚኮ በሰው ሃብት ልማት ዘርፍ ያካበተው ትልቁ ስኬት ለአንድ ተቋማዊ ዓላማ በጋራ መቆም የሚችሉ ሠራተኞች መገንባትን ነው ይላሉ፡፡ የአሚኮ ሠራተኞች ከግል ፍላጎት ይልቅ ለሕዝብ ጥቅም በጋራ መቆም፣ በአንድ ተቋም ጥላ ሥር ለተመሳሳይ ዓለማ በጋራ መሰባሰብ፣ ችግር ባለባቸው አካባቢዎ ሁሉ ቀድሞ በመድረስ ለሕዝብ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ መስጠት እና የሕዝብ ጥቅም እና መብትን ማስከበር መለያዎቻቸው ኾኗል ነው ያሉት፡፡ ይህ ጥረትም ተቋማዊ ቅቡልነትን እና ሕዝባዊ መሠረትን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
አሚኮ የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት የጣሉበትን ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እየሠራ ነው ያሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ በቀጣይም ጥራት እና ተደራሽነት የተቋሙ ስኬት መለኪያዎች ኾነው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ ተዓማኒነቱን፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እና አገልጋይነቱን አስጠብቆ ለመቀጠልም የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!