የሀገሪቱ የወጭ ንግድ 13 በመቶ ማደጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ፡፡

154

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው የሀገሪቱ የወጭ ንግድ ማሽቆልቆል መቀልበሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ዐብይ በማብራሪያቸው “የወጪ ንግዱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራና በሌሎች ዘርፎች የነበረውን ጉድለት ለመሙላት እገዛ አድርጓል” ብለዋል፡፡ ባለፉት 10 ወራት ከቡና 667 ሚሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ መገኘቱንና 16 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንም በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም ዓቀፍ ገበያ የቡና ምርት ፍላጎት እና ዋጋ መጨመሩ፣ ከዚህ በፊት ምርቱን ይልኩ የነበሩ ሀገራት በወረርሽኙ ምክንያት ፍላጎታቸው መቀዛቀዙ እና ኢትዮጵያ ባላት አቅም ለውጭ ገበያ ማቅረቧ እድሉን ለመጠቀም እንዳስቻላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በጎረቤት ሀገራት መቀዛቀዝ ከታየበት የአበባ ምርት የወጪ ንግድ ደግሞ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት 440 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን፤ ዘርፉም 84 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አብራርተዋል፡፡ ከስጋ ደግሞ 45 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘና በዘርፉም 20 በመቶ እድገት መመዝገቡን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ያስረዱት፡፡

በሽታው በኢትዮጵያ ውስጥ የሰፋ ስላልነበረ እና የሚያኮራ አየር መንገድ መኖሩ ለዘርፉ እድገት የጎላ ሚና እንደነበረውም ዶክተር ዐብይ ጠቅሰዋል፡፡ በማዕድን ዘርፍ በተለይ ወርቅ በኮንትሮባንድ እና የተለያዩ ምክንያቶች እያሽቆለቆለ እንደነበር በማስታዎስም ከኮሮናቫይረስ መከሰት በኋላ በሦስት ሳምንታት ብቻ 800 ኪሎ ግራም ገደማ ወርቅ ወደ መጠባበቂያ መግባቱን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 10 ወራት 27 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ ገቢ እንደተደረገ፣ ይህም 19 በመቶ እድገት እንዳለው አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ስኬቶች መመዝገባቸው አጠቃላይ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ 13 በመቶ እንዲያድግ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ “ከእድገቱ በተጨማሪ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው የወጭ ንግድ እድገት ማሽቆልቆል እንደተቀለበሰም አብራርተዋል፡፡

በገቢ ንግድ በኩል ደግሞ ነዳጅ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አስታውቀዋል፤ ከዘርፉ በ100 ሚሊዮኖች የሚገመት ዶላር ማትረፍ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን እንደ መድኃኒት፣ የአፈር ማዳበሪያ እና መሰል ወሳኝ ምርቶች የገቢ ንግድ አለመቀዛቀዙን፣ ይልቁንም የበለጠ መጨመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በየማነብርሃን ጌታቸው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየጣና ሐይቅን መታደግ ካልተቻለ ሌሎች ፕሮጀክቶችም አደጋ እንደሚገጥማቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳሰቡ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ 136 ተጨማሪ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፡፡