
በሰላም እጦት ምክንያት ትውልዱ ላይ የተራዘመ ጉዳት እንዳይደርስ መሥራት ይገባል።
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ዘርፋ ላይ የደረሱ ችግሮችን በመለየት የማካካሻ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል።
የተዘጋጀውን እቅድ አስመልክቶም ከትምህርት አጋር እና ባለ ድርሻ አካላት ጋር መግባባት የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጸጋዬ እንግዳ ወርቅ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በዘለቀው የሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው በመኾኑ ከመማር ማስተማር ሥራ ውጭ መኾናቸውን ተናግረዋል ።
በሰሜን ሸዋ ዞን በ2017 የትምህርት ዘመን ብቻ 407 ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራ ውጭ እንደነበሩ ነው የገለጹት። በዚህ ምክንያትም ከ380 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም ነው ያሉት።
ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎች ለሕገ ወጥ ስደት፣ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለሥነ ልቦና ችግር ተጋላጭ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ለመኾን ተተኪውን ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት የመገንባት ጉዞው “በሰላም እጦት ምክንያት የተራዘመ ጉዳት እንዳያስከትል መሥራት ይገባልም” ብለዋል ኀላፊው።
በ2018 የትምህርት ዘመን በሰሜን ሸዋ ዞን ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ነው የገለጹት።
ከነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ የተሟላ ምዝገባ በማካሄድ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መርሐ ግብር መሠረት ከመስከረም 5/2018 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መደበኛ ትምህርት ይጀምራል ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን ገጽታ የማሻሻል፣ ግብዓት የማሟላት እና ተያያዥ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ኀላፊው አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት በማስቆም ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን