
አሚኮ የምክር ቤት ጉባኤዎችን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል።
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት የሕዝብ ድምጽ በመኾን ደማቅ ታሪክ ጽፏል። የመረጃ ምንጭ ባልነበረበት እና እንደ አሁኑ የሚዲያ አማራጭ ባልሰፋበት ወቅት የሕዝብ ልሳን ኾኖ አገልግሏል።
በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ከዚህ ዘመን የደረሰው አሚኮ ዛሬም ለኀብረተሰብ ለውጥ እየተጋ ይገኛል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሀናን አብዱ አሚኮ ምክር ቤቱ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ እየገባ አብሮን ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
አሚኮ የምክር ቤት ጉባኤዎችን በመከታተል ለሕዝብ ተደራሽ ሲያደርግ የቆየ የምክር ቤቶቻችን እና የአማራ ሕዝብ ልሳን ነው ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አድና ምህረት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የምክር ቤት ጉባኤዎችም ኾነ ሌሎች ተግባራት ከአጋርነት ባለፈ ባለቤት ኾኖ እየሠራ ያለ ተቋም ስለመኾኑም ነው የሚናገሩት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በየደረጃው የሚደረጉ የምክር ቤት ጉባኤዎችን ለሕዝቡ ተደራሽ እንዲኾኑ በኀላፊነት እየሠራ እና አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደኾነም ገልጸዋል።
የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሲያጋጥሙም የሕዝቡን ፋላጎት እና ጥያቄዎች ወደ ዓደባባይ በማውጣት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
ወደ ፊትም የአገልግሎት አድማሱን እና ተደራሽነቱን በማስፋት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉትን ጸጋዎች አጉልቶ ለማውጣት ጥረት እንደሚያደርግ ተስፋ እናደርጋለን ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጌትነት እውነቱ በበኩላቸው አሚኮ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እየፈጸመ ያለ ተቋም ነው ብለዋል። ለሀገራችን ሞዴል መኾን የሚችል ተቋም ነውም ይላሉ።
በምክር ቤቶች የሚካሄዱትን ጉባኤዎች ተከታትሎ የዘገባ ሽፋን በመሥጠት የማይተካ ሚና ተጫውቷል ብለዋል። በአስፈጻሚው አካል የሚታየውን ጉድለት ለይቶ ወደ ሕዝብ በማድረስ እና በየደረጃው የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
አሚኮ የጀመረውን ለውጥ አጠናከሮ፣ የበለጠ ዘምኖ፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት እያጎለበተ በመቀጠል ለክልላችን ልማት የድርሻውን እንዲወጣም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን