የወልድያ-ፍላቂት መንገድን መልሶ ለመገንባት እየተሠራ ነው።

16

የወልድያ-ፍላቂት መንገድን መልሶ ለመገንባት እየተሠራ ነው።

ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ-ፍላቂት መንገድ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተ የጸጥታ ችግር ምክንያት የተስተጓጎለ ቢኾንም መልሶ ግንባታ ሥራውን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የኮምቦልቻ መንገድ አውታር ማኔጅመንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የመንገድ ጥገና፣ የድልድይ መልሶ ግንባታ እና ጥገና ሥራዎችን በማከናዎን ላይ ነው የሚገኘው።

ከእነዚህም ሥራዎች መካከል የወልድያ-ፍላቂት ከባድ ጥገና ፕሮጀክት አንዱ ሲኾን ፕሮጀክቱ ሕዳር 2011 ዓ.ም በኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የከባድ ጥገና ሥራ ተጀምሮ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የአስፋልት ንጣፍ ሥራውም 20 ኪሎ ሜትር በ10 ሳንቲሜትር ውፍረት እንዲሁም የድልድይ ጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።

ኾኖም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሥራ ተቋራጩ ለሥራ ያስገባቸውን ማሽኖች እና ፕላንቶች ወድመዋል።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞም መንገዱ ተጨማሪ ከፍተኛ ጉዳት በማስተናገዱ የመልሶ ግንባታ ዲዛይን እንደ አዲስ እንዲሠራለት ዕቅድ ተይዞ የዲዛይን አማካሪ ቅጥር በሂደት ላይ ይገኛል ነው የተባለው።

የዋናው መልሶ ግንባታ ሥራ እስከሚጀመር ድረስም የትራፊክ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ በ2017 በጀት ዓመት የጥቁር ውኃ ድልድይን ጨምሮ ጥገና በማድረግ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፡፡

የጊምቦራ ድልድይም ያጋጠመውን የመሸርሸር አደጋ የመከላከል ሥራም ተሠርቷል ነው የተባለው።

በሥራው ላይ ረዥም ርቀት ላይ የሚገኙ ግብዓቶችን ለመጠቀም የጸጥታ፣ የወሰን ማስከበር ሥራ ችግር እና ዝናቡ ከወትሮ በተለየ መልኩ ቀድሞ በሰኔ ወር መጀመሩ በችግሮች ተጠቅሷል፡፡

በ2018 በጀት ዓመትም አስፈላጊው በጀት በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ተመድቦ የተጎዱ መንገዶችን በፍጥነት በመጠገን የትራፊክ ሂደቱን ለማሳለጥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የጉዳት መጠን 50 በመቶ ለመቀነስ እየተሠራ ነው።
Next article“አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ስሌት ነው በሚል የሚዘዋወረው መረጃ ስህተት ነው” የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽኝ