በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የጉዳት መጠን 50 በመቶ ለመቀነስ እየተሠራ ነው።

16
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ባለሥልጣን በመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 557/2016 አተገባበር ላይ የተገኙ ለውጦችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ወርቁ ያየህ ኢትዮጵያ አነስተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ቢኖራትም የሚደርሰው አደጋ ግን ከፍተኛ ነው ብለዋል። ከሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ውስጥ 83 በመቶ የሚኾነውን ድርሻ የሚይዘው ከአሽከርካሪ እና ከተሽከርካሪ ብቃት ችግር ጋር ተያይዞ የሚከሰት እንደኾነ ነው የገለጹት።
እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2030 ባለው ጊዜ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የጉዳት መጠን 50 በመቶ ለመቀነስ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ አዲሱ የትራፊክ ደንብ ቁጥር 557/2016 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ እየተሠራበት ይገኛል ነው ያሉት።
በክልሉ የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ብቃትን ለማረጋገጥ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ሶፍትዌር በማበልጸግ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በ14 ማዕከላት ላይ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ አገልግሎት እየተሠጠ መኾኑንም አንስተዋል።
በተሠራው ሥራም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ትራፊክ ቅነሳ ኢላማ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሞተረኛ እና የቪአይፒ ቁጥጥር ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር አርጋቸው ረጋሳ የተሻሻለው ደንብ ከዚህ በፊት ከነበረው ደንብ አስተማሪ ቅጣቶችን የያዘ ነው ብለዋል። በደንቡ ተጨማሪ ወንበር፣ ከታሪፍ በላይ ክፍያ፣ የተሳፋሪዎችን እንግልት የመሳሰሉ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት መነሐሪያ ውስጥ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን የተመለከቱ ቅጣቶች መካተት እንዳለባቸው አንስተዋል።
የመንገድ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ከፖሊስ እና ትራንስፖርት ባለሙያው ባለፈ ማኅበረሰቡ በራሱ ሕግን አክብሮ የማስከበር ተግባር መሥራት ይገባዋል ብለዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የሲቪል እና ውኃ ሃብት ምህንድስና፣ የመንገድ እና ትራንስፖርት ትምህርት ክፍል ኀላፊ እና መምህር ተስፋሁን ንጋቱ የወጣው ደንብ በመንገድ ደኅንነት ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል። እስከ አሁን በነበረው የትግበራ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን፣ መልካም ሥራዎችን እና በቀጣይ ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮችን ግብዓት የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል። የተለዩትን ደግሞ በመተንተን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል።
ደንቡ የትራፊክ ደኅንነቱን በማስጠበቅ ከፍተኛ ለውጥ ቢያመጣም አሁንም ግን በአሽከርካሪዎች፣ በተሳፋሪዎች እና አልፎ አልፎ በፈጻሚዎች በኩል የአተገባበር ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። የመንገድ ትራንስፖርትን ደኅንነት በተሟላ መንገድ ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ኀላፊነት ወስደው እንዲሠሩም ጠይቀዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት የሥራ ሂደት ቡድን መሪ ብርሃኔ አበበ ደንቡ ጥፋተኞችን ማረም የሚያስችል፣ አዳዲስ ቅጣቶችን ያካተተ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኮምቦልቻ ከተማ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን አስጀመረ።
Next articleየወልድያ-ፍላቂት መንገድን መልሶ ለመገንባት እየተሠራ ነው።