የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኮምቦልቻ ከተማ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን አስጀመረ።

13
ደሴ: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኮምቦልቻ ከተማ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለመገንባት ሥራ አስጀምሯል። ለተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በአዲስ መልክ የቤታቸው ግንባታ ሥራ ከተጀመረላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ መሰሉ ዮሐንስ ከልጆቻቸው ጋር ሊወድቅ በደረሰ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር። በዚህም ምንያት በክረምት ለዝናብ እና ብርድ፣ በበጋ ወቅት ደግሞ ለፀሐይ እና ነፋስ በመጋለጥ ለጤና ችግር ይዳረጉ እንደነበር ጠቁመዋል። አሁን ላይ ቤታቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሊገነባላቸው መኾኑን ሲሰሙ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ የቤታቸው የግንባታ ሥራ በመጀመሩም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አወል በሽር ለልጃቸው የትምህርት ቁሳቁስ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል። የደብተር፣ እስክርቢቶ እና የቦርሳ ድጋፍ ማግኘታቸው ጭንቀታቸውን እንደሚያቃልልላቸው ነው የተናገሩት። የኮምቦቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሥራ አሥኪያጅ አህመድ ሠይድ ለተማሪዎች የተደረገው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው ብለዋል። የኢኮኖሚ ዞኑ ለሚገኝበት አካባቢ በተለያየ መልኩ የማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ.ር) ኮርፖሬሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት ተልኮ ባሻገር በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት መገንባት እና ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ዛሬም በኮምቦልቻ ከተማ ለ150 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። ለአቅመ ደካሞችም ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሥራ ማስጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡ ግንባታውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም በማጠናቀቅ ለግለሰቦቹ እንደሚያስረክቡም ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ ከሚያገኘው ትርፍ ውስጥ ሁለት በመቶውን ለማኅበራዊ አገልግሎት ከማዋልም ባሻገር ከሌሎች አጋር አካት ጋር በመተባበር ኀላፊነቱን ይወጣል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበበጀት ዓመቱ የሕዝብ ውክልና ኀላፊነትን ለመወጣት በትኩረት ይሠራል።
Next articleበትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የጉዳት መጠን 50 በመቶ ለመቀነስ እየተሠራ ነው።