
ደብረ ታቦር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር በዓል በደብረ ታቦር ኢየሱስ ተራራ ነው በድምቀት የተከበረው።
መንፈስን የሚያድሰው አንዱ የበዓሉ ትልቅ ገጽታ ተክሌ አቋቋም ዝማሜ በሊቃውንቱ ቀርቧል። ሌሎች ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችም ተካሂደዋል።
ደብረ ታቦር ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ውስጥ ካለው የታቦር ተራራ ጋር ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገሮች እንዳሉ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ። የደብረ ታቦር ከተማ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል ኀላፊ በኲረ ትጉሃን መምህር ሁልጊዜ ዓለማየሁ እንዳስገነዘቡት ደብረ ታቦር በነብያት ብዙ ጊዜ የተነገረለት በኋላም የነብያትን ሀሳብ ለመፈጸም ሰው የኾነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ የወጣበት ተራራ ነው።
ደብረ ታቦር ዘ-እስራኤል እና ደብረታቦር ዘ-ጎንደር የሚያመሳስላቸው ስም ብቻ ሳይኾን የታሪክ ሁነታቸው እና ተግባርም ጭምር ነው ሲሉም ነግረውናል። በዓሉ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዓበይት ዘጠኝ በዓላት መካከል አንዱ ነው። ማኅበረሰቡ በዓሉን ጠብቆ በማክበር ለትውልድ ማስረከብ አለበት ያሉት በኲረ ትጉሃን የአሁኑ ትውልድ ዘመኑን በመዋጀት ከማንነት ሳይወጣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር የሚጠቅመውን በማስቀጠል የአባቶችን ፈለግ እንዲከተል ጥሪ አቅርበዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች በዓሉ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዞ እንዲቀጥል ሳይበረዝ ማክበር ይገባል ብለዋል። ትውልዱም የሃይማኖት እና ሀገር ተረካቢ በመኾኑ ታሪክን ማወቅ እና ማስቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት። በዓሉን ለትውልድ ለማስቀጠል የማኅበረሰቡ ድርሻ ጉልህ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ልጆች የቡሄ ጭፈራን በሚጨፍሩበት ወቅት የተለመደውን ባሕል የሚገልጸውን ስጦታ በማበርከት ሳይበረዝ ማስቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን