
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) መንግሥት አሳሳቢነቱን በመረዳት ከአውሮፓ የተሻለ ማሽን ለመግዛትና በሰው ኃይል ታግዞ ለማስወገድ በጊዜያዊነት እየተሠራ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) አስታውቀዋል፡፡
የጣና ሐይቅን በእምቦጭ አረም መወረርና እየተወሰዱ ያሉ መፍትሔዎችን አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም እምቦጭን መጀመሪያ በሰው ኃይልና በማሽን ማስወገድ ጊዜያዊ መፍትሔ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ዘላቂው መፍትሔ ግን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ማጠናከር እንደሆነ ዶክተር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ተናግረዋል፡፡
የጣና ሐይቅና ተከዜ ወንዝ ተፋሰስ መነሻ የሆነው የጉና ተራራ አካባቢ መራቆት ካልተመለሰ እምቦጭን በዘላቂነት ማስወገድ እንደማይቻልም ነው በማብራሪያቸው ያመለከቱት፡፡ ከ4 ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው የጉና ተፋሰስን የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅና እንደ ርብ እና ጉማራ ያሉ ወንዞች ከፎገራና አካባቢ ወደ ጣና ሐይቅ የሚያስገቡትን የእምቦጩን ምግብ ማስቀረት እንደሚገባም መክረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት እምቦጭን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር እየሠራ እንደሆነና በቅርቡ ውይይት ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም የክልሉን ጥረት ለማገዝ ከአውሮፓ የተሻለ ማሽን ለመግዛት እየተደራደረ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ዘላቂ መፍትሔው ግን የተፈጥሮ ሀብቱን መታደግና ማልማት እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ አምስት ቢሊዮን ችግኝ የመትከል የዚህ ዓመት መርሀ ግብር የተፈጥሮ ሀብቱን ለመታደግ አጋዥ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የተፈጥሮ ሀብቱን መንከባከብ ሲቻል ወደ ጣና ሐይቅም ሆነ ወደ ሌሎችም ውኃማ አካላት የሚመጣውን እምቦጭ አረምና ሌሎችንም ችግሮች መመከት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ጣና ሐይቅን አለመታደግ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም አደጋ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዐብይ ‘‘ጣናን ካልታደግን ሌሎች ፕሮጀክቶችም አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውኃ ምንጭም ነውና’’ ሲሉም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በአብርሃም በዕውቀት
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡