አሚኮ ለብሔረሰቦች ሁለንተናዊ እድገት አቅም የኾነ ሚዲያ ነው።

17
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ከተመሠረተበት 1987 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሚዲየሞች የቋንቋ፣ የአየር ጊዜ እና የተደራሽነት ሽፋኑን በማሳደግ እያገለገለ ያለ የሕዝብ ሃብት ነው።
በ”በኩር” ጋዜጣ የተጀመረው አገልግሎት በ30 ዓመት ጉዞው በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ፣ በኤፍ ኤም፣ በጋዜጣ እና በዲጂታል ሚዲያ አድማሱን ያሰፋ ግዙፍ ሚዲያ ኾኗል። አሁን ላይ ሁለት የውጭ ቋንቋዎችን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋን የሚሰጠው አሚኮ ለክልሉ ብሔረሰቦችም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ለኽምጣና፣ ለአዊኛ እና ለኦሮሞ ብሔረሰብ ቋንቋዎችም የቴሌቪዥን፣ የሬድዮ፣ የጋዜጣ እና የዲጂታል ሚዲያ ሽፋን በመስጠት መረጃ በሰፊው እያደረሰ ይገኛል።
ለብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚዲያ ሽፋን መስጠት ዴሞክራሲያዊ መብትን ከማክበርም በላይ በሀገራቸው ምጣኔ ሃብት እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ላይ ንቁ ተሳታፊ ኾነው እንዲያድጉ ማገዝ መኾኑን ነው አስተያየት ሰጭዎች የተናገሩት። በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕምጣና ቋንቋ ዜና እና ፕሮግራሞች ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ወንድሙ ቸኮለ አሚኮ በአማራ ክልል ውስጥ በሚነገሩ የብሔረሰብ ቋንቋዎች ስርጭት ማድረጉ የክልሉን ገጽታ ለማስተዋወቅ እና የብሔረሰቦችን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ መስጠት ያስቻለ ነው ብሏል።
አሚኮ በጋዜጣ፣ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን እና በዲጂታል ሚዲያ ዜና እና ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ የዋግ ብሔረሰብ ቋንቋውን የመጠቀም፣ የማሳደግ እንዲሁም ሃሳቡን የመግለጽ መብቱን እንዲተገብር እያገዘ መኾኑንም አንስቷል። እኛ የዋግ ሕዝብን ቋንቋ፣ ባሕል፣ ትውፊት፣ ታሪክ በአጠቃላይ ማንነቱን ለመግለጽ በሚዲያው ስንሠራ ቋንቋውን የሚናገሩ፣ የሚያዳምጡ እና የሚያነቡ ሰዎች ግብዓቶች እየሰጡን ነው። ለዚህም የአሚኮ አስተዋጽኦ ከፍተኛነት ነው ብሏል ጋዜጠኛ ወንድሙ። አሚኮ ከክልል ሚዲያዎች ቀዳሚ ኾኖ በብሔረሰቦች ቋንቋዎች መሥራቱ ረጅም ራዕይ ያለው መኾኑን ያመለክታል ነው ያለው። ብሔር ብሔረሰቦችም በሚዲያው የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው አድርጓል ሲልም ገልጿል።
ሻደይን ጨምሮ የተለያዩ የዋግ ብሔረሰብን የሚያስተዋውቁ ፕሮግራሞችን ሢሠራ መቆየቱን የጠቀሰው ጋዜጠኛ ወንድሙ ሕዝባዊ በዓላትን፣ ታሪክን እና ባሕልን በቋንቋው በማክበር ለዋግ ሕዝብ ማንነት መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ገልጿል። በብሔረሰብ ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋን የሚሰጥበት የአየር ጊዜው እያደገ መኾኑንም አንስቷል። የሰቆጣ ኤፍ ኤም ግንባታ ተጠናቅቆ ቁሳቁስ መሟላት ብቻ እንደቀረው የተናገረው ጋዜጠኛ ወንድሙ በቅርቡ ሥራ ሲጀምርም የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ሕዝብ በሕምጣና ቋንቋ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንደሚኖረው ገልጿል።
ሌላው አስተያየት ሰጭ ጋዜጠኛ ፍሬዘር አድማስ ቋንቋ ለአንድ ማኅበረሰብ ባሕል ማደግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብሏል። ቋንቋው በሚዲያ ሥራ ላይ ሲውል ማኅበረሰቡ ራሱን ለመግለጽ፣ ባሕሉን ለማዳበር እና ለማጉላት ትልቅ መሣሪያ እንደኾነ ነው የገለጸው። አሚኮ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋን መስጠቱ ሕዝቦች ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውን እና ማንነታቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጿል። እናም አሚኮ ለክልሉ ብሔረሰቦች ማንነት መጎልበት እየሠራ መኾኑን አንስቷል። ቋንቋ ባሕልን፣ ማንነትን እና ታሪክን የመሰሉ እሴቶችን ያቀፈ በመኾኑ ለአንድ ማኅበሰረብ መሠረታዊ እንደኾነ ነው የገለጸው። የሥልጣኔ መነሻ እና ማስተላለፊያም ነው ብሏል። አሚኮም ብሔረሰቦች ይህንን ሃብት እንዲያዳብሩት እየረዳ ነው ብሏል ጋዜጠኛ ፍሬዘር።
በአፋን ኦሮሞ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች በክልሉ ውስጥ ብቻ ሳይኾን ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ ሕዝቦችም ትክክለኛውን መረጃ በማሳወቅ ወንድማማችነት እና አንድነት እንዲፈጠር እየሠራ መኾኑን ገልጿል። ማኅበራዊ ትስስርን፣ የጋራ ታሪክ እና እሴትን በመግለጽ ከክልሉም አልፎ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አሚኮ በትጋት እየሠራ መኾኑንም ጋዜጠኛ ፍሬዘር ጠቅሷል። አሚኮ በብሔረሰብ ቋንቋዎች ዜና፣ ፕሮግራሞች፣ ማስታወቂያ፣ መዝናኛ እና ሌሎች ዝግጅቶችን ሲያሰራጭ በቋንቋው እና በባሕሉ ተመስርቶ በመኾኑ የብሔረሰቡ ሁለንተናዊ እድገት እንደሚፋጠን አንስቷል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለፉት 30 ዓመታት ለአዊ ሕዝብ ብዝኃ ሥራዎችን በማከናወን በኩል ባለውለታ መኾኑን የተናገረችው ደግሞ በኮርፖሬሽኑ የአዊኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ይፍቱሥራ ፈንታሁን ናት፡፡
አሚኮ ከምሥረታው ጀምሮ ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይኾን ለመላው ኢትዮጵያውያን እና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ተከታዮችም በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ነው ያለችው። አሚኮ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች ቋንቋቸው እንዲያድግ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል ብላለች።
አሚኮ በተለይም የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር ሕዝብ ማኅበራዊ ሕይዎቱን፣ ባሕሉን፣ ወጉን፣ እሴቱን እና ትውፊቱን ከማሳደግ አንጻር በርካታ ሥራዎችን አበርክቷል ነው ያለችው፡፡ በ1997 ዓ.ም በአዊኛ ቋንቋ ለ15 ደቂቃ በራዲዮ ስርጭት ወደ ማኅበረሰቡ መድረስ መጀመሩን ያስታወሰችው ዳይሬክተሯ በየጊዜውም ማሻሻያዎችን እና አዳጊ ሥራዎች መከናዎናቸውንም አንስታለች፡፡ አሁን ላይ በጋዜጣ፣ በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በዲጂታል ዘርፎች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ነው ያለችው፡፡
ዘጋቢ: ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን አስጀመሩ።
Next articleየትውልዱ አደራ!