
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዘመናዊ ጥበብ ፈር ቀዳጁ አርቲስት ደበበ እሸቱ አስክሬን ሽኝት መርሐ ግብር በብሔራዊ ቴዓትር እየተካሄደ ነው።
በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ ሌሎችም ሚኒስትሮች እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1934 ዓ.ም እንደተወለደ ታሪኩ ይናገራል። አርቲስቱ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም እና በጋዜጠኝነት ሙያ በርካታ ሥራዎችን ለአድማጭ ተመልካች ማድረስ ችሏል፡፡
ተዋናይ፣ ኮሜዲያን እና አዘጋጅ ኾኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው አርቲስቱ በቴአትር መድረኮች በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የኾኑ ሥራዎችን በማቅረብ ይታወሳል፡፡ አርቲስት ደበበ በሀገር ፍቅር እና በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ለበርካታ ዓመታት በተዋናይነት እና በአዘጋጅነት ሠርቷል። ጋሽ ደበበ በብሔራዊ ቴአትር ለ22 ዓመታት አገልግሏል። በራስ ቴዓትርም ሥራ አስኪያጅ ኾኖ ሠርቷል። ኢትዮጵያን ወክሎም የተለያዩ አሕጉራዊ ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፏል። ከ40 በላይ ተውኔቶች ላይ ሠርቷል። ከተወኑባቸው ቴአትሮች መካከል እናት ዓለም ጠኑ፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ኪንግ ሊር፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ የከርሞ ሰው እና ጠልፎ በኪሴ የሚሉት ይገኙበታል።
የመንግሥቱ ለማን “ጠያቂ”፣ የተስፋዬ ገሰሰን “ተሐድሶ”፣ የአያልነህ ሙላትን “ሻጥር በየፈርጁ”፣ የነጋሽ ገብረማርያምን “የአዛውንቶች ክበብ” እና የዊልያም ሼክስፔርን “ሊር ነጋሲን” ጨምሮ 28 ተውኔቶችን አዘጋጅተው ለዕይታ አቅርቧል። በፊልም ሥራም የተለያዩ በኢትዮጵያውያን የተዘጋጁ የሀገር ውስጥ ፊልሞችን ጨምሮ “Shaft in Africa”፣ “The African spy”፣ “The Sailor from Gibraltar”፣ “A Season in Hell”፣ “Zelda”፣ “The gravedigger”፣ “The grand rebellion” እና “Red Leaves” በሚሉት ላይም ተሳትፏል። በሥነ ጽሑፍ ዘርፍም ከተዋናይ ሀሁ፤ የባሩድ በርሜል፤ ድብልቅልቅ የመድረክ ተውኔት፣ ያልታመመው በሽተኛ፣ የደም እንባን እና ሌሎችንም ሥራዎች ወደ አማርኛ ተርጉሟል።
ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ የአፍሪካ መድረክ ባለሙያዎች ማኅበር መስራች፣ የዓለም ኮንቴምፖራሪ ቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባል፤ የዓለም አቀፍ ቴአትር ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ አስተባባሪ እና የኢትዮጵያ ተጠሪ፤ በብሔራዊ ቴአትር የፕሮግራም እና ፕሮዳክሽን ኀላፊ፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር የኪነ-ጥበብ አገልግሎት ኀላፊ እና በራስ ቴዓትር ዋና ሥራ አሥኪያጅ ነበር። በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን በርካታ ማኅበራዊ፣ የልማት እና እርዳታ አገልግሎቶችን ላይ አስተባባሪ፣ የሰላም እና እርቅ ኮሚቴ አባል፣ የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል አምባሳደር እና “በኩላሊት ሞት ይብቃ” አምባሳደር በመኾን አገልግሏል። አርቲስት ደበበ በበጎ ፈቃድ ሥራዎችም ግንባር ቀደም ነበር። በሀገር ላይ ችግር ሲከሰት ከፊት በመቆም በርካታ አስተዋጽኦ ያበረከተ እንደነበር አርቲስትና ጓደኛው ተፈሪ ዓለሙ በሕይዎት ታሪኩ ንባብ ላይ አቅርቧል። አርቲስት ደበበ እሸቱ የ4 ልጆችና 8 የልጅ ልጆች አባት ነው።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!