
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መለኮት የተገለጠበትን ተራራ ስም ወርሳለች። በተራራው የተፈጸመውን ድንቅ ነገር ጠብቃለች። ክብሩን አስከብራለች። ስሙን ጠርታለች። በስሙም ተጠርታለች። በክብሩም ከብራለች።
ሃይማኖትን ከታሪክ፣ ትውፊትን ከቃል ኪዳን ጋር አስተሳስራ ኖራለች። አጽንታም ዘመናትን ተሻግራለች። አበው የሠሩትን ሥርዓት አላፈረሰችም። አበው ያኖሩትን ቃል ኪዳን አልተወችም። የትናንቱን እየጠበቀች፣ የአበውን ሥርዓት እያስተማረች፣ ለልጅ ልጅም እያወረሰች ኖረች እንጂ። ተራራዎቿ ሃይማኖት ይሰበክባቸዋል። ሊቃውንት ይፈልቁባቸዋል። ነገሥታቱ ዙፋናቸውን ያጸኑባቸዋል። ጎበዛዝቱ በክብር ይኖሩባቸዋል። ከተራራዎቿ አናት ላይ የሚገኙ አድባራት ይባርኳታል። ይጠብቋታል። ክብር እና ሞገስን ይሰጧታል። በረከት እና ረድኤት ይዘንብላታል።
ጠቢባኑ ጥበብን ይዘሩባታል። ደጋጎቹ በደግነት ይኖሩባታል።
በብርሃን ተራራ የተሰየመች። በብርሃን ተራራ ክብር የጸናች። በብርሃን ተራራ ሞገስን የተቸረች። በብርሃን አምላክ የተጠበቀች። በብርሃን ልጆች የከበረች የሊቃውንቱ መዳረሻ፣ የነገሥታቱ መናገሻ ናት ደብረታቦር። ደብረታቦር የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የባሕል እና የእሴት ከተማ ናት። የከበቧት ተራራዎች ታሪክ እና ሃይማኖትን አስተባብረው ይኖራሉ። ለደረሰው ሁሉ የጥንቱን ታሪክ ይነግራሉ። ነዋሪዎቿ እሴት እና ባሕልን ይጠብቃሉ። እልፍኛቸውን አስተካክለው፣ አዳራሻቸውን አሳምረው እንግዳ ይቀበላሉ። በትህትና ያስተናግዳሉ። በፍቅር ይሸኛሉ።
ይህች በሠርክ ታሪክ እና ሃይማኖት የሚነገርባት ከተማ በበዓለ ደብረታቦር ትደምቃለች። ጎዳናዎቿን ታሰማምራለች። ነጫጭ በለበሱ አማኞች ትዋባለች። በሊቃውንት ዝማሬ እና ጸሎት ትሞላለች። በእልልታ እና በውዳሴ ትዋጣለች። በበዓለ ደብረታቦር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረታቦር ተራራ ያደረገውን፣ የገለጠውን ምስጢር፣ ጌትነቱን፣ አምላክነቱን እና መለኮቱን እየነገረች ትኖራለች። አበውም ስለ በዓለ ደብረታቦር ያስተምራሉ። በበዓለ ደብረታቦር የተገለጠውን ይሰብካሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ታቦር ኢየሱስ እና የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ አድባራት ስብከተ ወንጌል ኀላፊ እና የሐዲስ ኪዳን እና የቅኔ መምህር መጋቢ ምስጢር መምህር ኤፍሬም ቢራራ በዓለ ደብረታቦር ስንል አንድም ቦታውን ማለታችን ነው፣ ሁለትም በዓሉን ማለታችን ነው ይላሉ። ደብር እና ታቦር ከሚሉ ቃላት የተገኘው ደብረታቦር ምስጢራዊ ፍቹ ሲመረመር ደብር ማለት ተራራ፣ ከፍታ፣ የሚታይ የሚያሳይ ማለት ነው። የሚያሳይ ሲባል ከተራራው አናት ለወጣ አካባቢውን የሚያሳይ ነው። የሚታይ ሲባልም በርቀት ኾነው በከፍታ የሚያዩት ማለት ነው።
ታቦር የሚለው ትርጓሜም ብርሃን ማለት ነው። ደብረ ታቦር ማለትም የብርሃን ተራራ ወይም ብርሃን የተገለጠበት ተራራ ማለት ነው ይላሉ።
በብሉይ ኪዳን በደብረታቦር ተራራ ዲቦራ እና ባርቅ ሲሣራ የተባሉ የእግዚአብሔር ባለሟሎች ጠላታቸውን ድል ነስተውበታል። በሐዲስ ኪዳንም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረታቦር ተራራ ላይ ጠላት ዲያብሎስን ድል ነስቶበታል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለያየትን አጥፍቶ አንድነትን ያጸናበት በዓል ነውና የአንድነት በዓል እየተባለም ይጠራል ይላሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን እና ያዕቆብን እንዲሁም ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ። ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ። ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ኾነ። እነሆም ከሙታን ወገን ሙሴ እና ከብሔረ ሕያዋን ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚህ መኾን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ አለ።
እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው። እነሆም ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ዐይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም ተብሎ እንደተጻፈ ደብረታቦር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብረ መንግሥቱን ግርማ መለኮቱን የገለጠበት ነው ይላሉ።
እግዚአብሔር በደብረታቦር ሙሴን ከመቃብር፣ ኤልያስን ከብሔረ ሔዋን አመጣቸው። ሦሥቱ ሐዋርያትንም ከሐዲስ ኪዳን የወሰዳቸው ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ይሄን ስለምን አደረገ የተባለ እንደኾነ ይላሉ መምህሩ ብሉይ ኪዳንን እና ሐዲስ ኪዳንን እንጀራ እና ወጥ አድርጎ ለማስማማት፣ ብሉይ ኪዳን እንዳልተሻረች ለማጠየቅ፣ የብሉያት እና የሐዲሳት ጌታ መኾኑን ለማሳየት ነው። ደብረታቦር የቤተክርስቲያንም ምሳሌ ናት። ወደ ተራራ ይዟቸው የወጣ አምስት ናቸው። ይሄም ለቤተክርስቲያን የሥርዓተ ቅዳሴ ምሳሌ ነው። ሥርዓተ ቅዳሴ በሦስት ዲያቆናት በሁለት ካህናት ይፈጸማልና። ከብሉይ ኪዳን የመጡት የቀሳውስት ምሳሌ፣ የሐዲስ ኪዳኖችም የዲያቆናት ምሳሌ ይኾናሉ ነው የሚሉት። ደብረታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌም ናት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት እና ባሕልን ጠብቃ ለትውልድ ታስተላልፋለች የሚሉት መምህሩ በበዓለ ደብረታቦርም ሃይማኖት እና ባሕል ይገለጣሉ። በበዓለ ደብረታቦር ነጭ ይለበሳል፣ ጅራፍ ይጮሃል፣ ሙልሙል ይጋገራል፣ የበግ ለምድም ይደረባል። ይህም እንደምን ኾነ ያሉ እንደኾነ ነጭ የሚለበሰው አምላክ በደብረታቦር ተራራ ላይ አብርቷልና ያን ለማስታወስ ነው። ስለ ምን ጅራፍ ይጮሃል የተባለ እንደኾነ በደብረታቦር የተሰማውን ድምጽ ለማጠየቅ ነው። የበግ ለምድ መልበስም በቀራንዮ ላይ እንደበግ ተሰውቶ የሰውን ልጅ ማዳኑን ለማመልከት ነው። ሙልሙል ዳቦውም ጌታ በደብረታቦር ብርሃኑን በገለጠበት ሰዓት እረኞች ሙልሙል ዳቦ ይዘው ነበር ያን ለማስታወስ የሚደረግ ነው። የችቦው መብራትም ጌታ ብርሃኑን በገለጠበት ጊዜ እረኞች ምሽቱም ቀን ስለመሰላቸው ወደቤታቸው አልተመለሱም ነበርና ወላጆቻቸው ልጆቻቸውን ፍለጋ ችቦ እያበሩ ስንቅም ሙልሙል ዳቦ ይዘው ሄደዋልና ያን ለማጠየቅ ነው።
እኔ ከሰማይ የወረድኩ የሕይወት ሕብስት ነኝ እንዳለ ሙሉሙል ዳቦው የሕይወት ሕብስትነቱን የሚያመላክት ነውም ይላሉ። በዓለ ደብረታቦር ቡሄ እየተባለ ይጠራል የሚሉት መምህሩ ቡሄ ማለት አንድም ሙልሙል ዳቦው ነው። በሌላ በኩልም ቡሄ ማለት ገላጣ ማለት ነው ይሉታል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየረር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የትርጓሜ መጻሕፍት መምህር መላከ ታቦር ኃይለኢየሱስ ፈንታሁን ደብረታቦር የእግዚአብሔር ተራራ፤ የጸና፤ የለመለመ፤ የረጋ ነው፤ እግዚአብሔር በወደደው ደብር ላይ ያድርበት ዘንድ የመረጠው ይሄ ነው ተብሎ አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለት ተራራ ነው ይላሉ።
ታቦር እና አርሞንዔም በአንተ ፊት ደስ ይላቸዋል ተብሎ እንደተጻፈም ደብረታቦር አስቀድሞ የተነገረለት ነው ይሉታል። አስቀድሞ ትንቢት እንደተነገረ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረታቦር ተራራ ላይ ትምህርተ መንግሥቱን፣ ክብሩን፣ ጌትነቱን ገልጧል፣ ቀን እና ሌሊቱን በብርሃን መልቷል ነው የሚሉት። በደብረታቦር ትምህርተ መንግሥቱን ስለገለጠ በዓሉ በቦታው ስም ይከበራል ይላሉ። ቅዱስ ጴጥሮስ የተቀደሰው ተራራ እንዳለ ሁሉ የደብረታቦር ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን የገለጠበት የተቀደሰ ተራራ ነው ይሉታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደብረታቦር የተገለጠውን ታምናለች። ታከብራለች። ኢየሩሳሌም እና ኢትዮጵያ እህታማች ናቸው የሚሉት መላከ ታቦር ይህም የጀመረው በንግሥተ ሳባ እና በጠቢቡ ሰሎሞን ነው። የኢትዮጵያ ነገሥታት ንግሥተ ሳባን መነሻ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ ቅዱሳት መካናትን ይጎበኙ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ከጎበኙት የኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል አጼ ሠይፈ አርድ አንደኛው ናቸው። በሀገረ እስራኤል አያሌ መካናትን ጎበኙ። በሀገረ እስራኤል የደብረታቦርን ተራራ ባዩ ጊዜ ደስ ተሰኙ። ይሄን የመሰለ ተራራ በሀገሬ ባገኝ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን አሰርቼ የእርሱን ጽላት አስገባለሁ ብለው ተሳሉ። ወደ ሀገራቸው ተነስተው የኢትዮጵያን ምድር ሲዞሩ በጌ ምድር ደረሱ። በኢየሩሳሌም ያዩትን ተራራ የሚመስል ተራራ ተመለከቱ። ስለታቸውን ፈጸሙ ይላሉ። ይህም ተራራ ደብረታቦር ኢየሱስ የታነጸበት ተራራው ነው።
በዓለ ደብረታቦር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይከበራል። ስሙን በወረሰችው በደብረታቦር ከተማ ደግሞ ከፍ ይላል።
መጋቢ ሚስጢር መምህር ኤፍሬም ቢራራም ሲናገሩ ደገኛው ንጉሥ አጼ ሠይፈአርድ ምድረ እስራኤልን ለመጎብኘት ሄደው ነበር። በዚያም በሄዱ ጊዜ እግዚአብሔር ግርማ መለኮቱን የገለጠበትን ደብረታቦርን ባዩ ጊዜ ተደነቁ። እሳቸውም ይሄን የመሰለ ሥፍራ በሀገሬ ባገኝስ ደብር እደብርበት፣ መታሰቢያውን አደርግበት ነበር ብለው ተሳሉ።
ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። በተመለሱም ጊዜ በፈረስ ላይ ተቀምጠው በሕዝብ ተከበው የኢትዮጵያን ምድር ይጎበኙ ነበር። በጌምድር በደረሱም ጊዜ በኢየሩሳሌም ያዩትን የደብረታቦርን ተራራ የሚመስል ተራራ ተመለከቱ። ያ ተራራስ ደብረታቦርን ይመስላል አሉ። ወደ ተራራውም ወጡ። ደብረታቦርም አሉት። እንደተሳሉትም በተራራው አናት ላይ ሕንጻ ቤተክርስቲያን አሠሩ። ታቦቱንም አስገቡ። በዚህም የከበረ ታሪክ ምክንያት በዓለ ደብረታቦር በደብረታቦር ደምቆ ይከበራል ነው ያሉት።
መላከ ታቦር ኃይለኢየሱስ ፈንታሁን ሲናገሩ የደብረታቦር ስያሜ በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን የተሰጠ ነው ይላሉ። ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ አባቱ ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ እስራኤላውያንን ይዞ ተመለሰ። ወደ ሀገሩ በተመለሰ ጊዜም ያስከተላቸውን ነገደ እስራኤልን ይዞ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ሰፍሮ ነበር። ቀዳማዊ ምኒልክን ተከትለው የመጡ ነገደ እስራኤላውያንም ወደ ከፍታ በወጡ ጊዜ የደብረታቦርን ተራራ ተመለከቱ። ይሄስ በሀገራችን ያለውን የደብረታቦርን ተራራ ይመስላል አሉ። በዚህም ምክንያት ደብረታቦር ተባለ ነው የሚሉት። ስሙም የወጣው የዛን ጊዜ ነው። በሙሉ ክብሩ ደብረታቦር ኢየሱስ የተባለው ግን በአጼ ሠይፈ አርድ ዘመነ መንግሥት ነው ይላሉ።
በዚህም ምክንያት በዓለ ደብረታቦር በደብረታቦር ደምቆ ይከበራል። ሊቃውንቱ እንደሚሉት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሃይማኖትን እና ባሕልን ይጠብቃሉና ከሁሉም በተለየ ሥርዓቱን ጠብቀው ያከብራሉ። ይዘክራሉ። የበረከቱም ተካፋይ ይኾናሉ። ኢትዮጵያ የያዘችውን ነገር የማትጥል፣ አንዱን ጥላ ሌላውን ተከትላ የማትሄድ ሀገር፣ አቋም ያላቸው ሕዝቦች ባለቤት መኾኗ የጥንቱን ይዛ ዘልቃለች ነው የሚሉት። ሥሪታቸው ሁሉ ሃይማኖታዊ ነው ይላሉ።
መላከ ታቦር ኃይለኢየሱስ ፈንታሁን ሲናገሩ በበዓለ ደብረታቦር በደብረታቦር ኢየሱስ የሚፈጸመውን ሥርዓት መናገር የሚቻለው አንደበት የለም ነው የሚሉት። ከተራራ ላይ በተሠራው ተራራ ላይ ሊቃውንቱ ድንቁን ሥርዓት ይፈጽማሉ፣ ሕጻናት እና አረጋውያን ነጭ ለብሰው በተራራው አናት ላይ ይከባሉ። እረኞች ይሰባሰባሉ። ይህም በታየ ጊዜ እጹብ ከማለት ውጭ ሌላ የሚገልጸው የለም ይላሉ። በዚያ ሥፍራ የረቀቀውን ሥርዓት ይፈጸማልና። ራስ ጉግሳ ደብረታቦር ኢየሱስን ላቂያዬ ይሉት ነበር። ይህ ላቂያ የኾነ ሥፍራ በበዓለ ደብረታቦር ይደምቃል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ማንነቱ ያልተቀየረ፣ ባሕሉ ያልተበረዘ ነውና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱም በነበረው ሥርዓት ይከበራል ነው የሚሉት።
እነኾ በዓለ ደብረታቦር ነውና ደብረታቦር በሊቃውንቱ ተከባለች። በአማኞቹ ተሞልታለች። ነጩን ካባ ተጎናጽፋለች። ከግርማ ላይ ግርማ ደርባለች። ከሞገስ ላይ ሞገስን አግኝታለች። ስሙን የወረሰችው፣ ክብሩን የጠበቀችው በተራራው አናት ላይ ለአምላኳ ምሥጋናን ታቀርባለች።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!