ዘመናዊ አሠራርን የሚፈልገው የኦፓል ምርት

38
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል በማዕድን ዘርፉ በርካታ ጸጋዎች አሉት። ክልሉ የኦፓል ማዕድንን ጨምሮ በርከት ያሉ ማዕድኖች የሚገኙበት ክልል እንደኾነ ይነገራል።
ኦፓል ከሚመረትባቸው የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ተጠቃሽ ነው። አቶ ደሳለኝ ሞላ በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን ማምረት ላይ ተሠማርተው ለ17 ዓመታት ሢሠሩ እንደቆዩ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። በዚህ ሥራ ሕይወታቸውን እየመሩበት ሲኾን ኑሯቸውም መሻሻሉን ነግረውናል። ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ እያስተማሩ ነው፤ ሌሎች ቤተሰቦቻቸውንም እንደሚደግፉ ነው የተናገሩት። ኦፓል የማኅበረሰቡን ሕይወት እየለወጠ የመጣ መኾኑን ገልጸዋል። በኦፓል ማምረት በርካታ ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል። ለወረዳው ሕዝብም የመኖር ዋስትናው እንደኾነ ነው የገለጹት።
ምርቱ በባሕላዊ መንገድ የሚመረት፣ በጥናት ያልተመረኮዘ እና ሳይንሳዊ ባልኾነ መንገድ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ሥራው ተጠንቶ ሳይንሳዊ ቢኾን ለአካባባቢው ማኅበረሰብም ኾነ ለሀገር የተሻለ ገቢ ይገኝበታል ነው ያሉት። ዘረፉ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ እና ተስፋ ሠጪ በመኾኑ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ምርታቸውን ሲሸጡ መሐል ላይ ደላሎች በመኖራቸው አምራቾች እና ላኪዎች በቀጥታ አለመገናኘታቸው ተጠቃሚነታቸውን እንደቀነሰውም ተናግረዋል። በወረዳው የኦፓል ምርቱን የሚያቀርቡበት የገበያ ማዕከል አለመኖሩ፣ የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ፣ ኦፓልን ዕሴት ጨምሮ የተሻለ ገቢ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጥር አለመደረጉንም እንደ ችግር አንስተዋል።
የደላንታ ወረዳ ማዕድን ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ሰማው የማዕድን ዘረፉ በወረዳው ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች ተሠማርተውበታል ብለዋል። ወጣቶች በ35 ማኅበራት ተደራጅተው ሕይወታቸውን እየመሩበት የሚገኝ ዘርፍ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ከተደራጁት በተጨማሪ በእሴት ሰንሰለት በርካታ የሥራ ዕድል የፈጠረ ዘርፍ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ ዘርፉ በ2017 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ማስገኘቱንም አንስተዋል። በወረዳው የሚገኘውን የኦፓል ምርት እሴት ጨምሮ የተሻለ የሥራ ዕድል እና ገቢ ለመፍጠር በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ኦፓልን በማስዋብ ሥራ የሠለጠኑ 101 ወጣቶች ወደ ሥራ ገብተው እየሠሩ ነው ብለዋል። የኦፓል ማስዋቢያ ማሠልጠኛ ማሽኖች በሰሜኑ ጦርነት መውደማቸው ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸውም ገልጸዋል።
በመሐል በሚገቡ ሕገ ወጥ ደላሎች ምክንያት ቀጥታ ከገዢዎች ጋር አለመገናኘት ያለውን ችግር ለመፍታት የገበያ ትስስር ሥራ መፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል። ለዚህም አካባቢውን እና ምርቱን ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው ወረዳው የሚችለውን እያደረገ ቢኾንም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አልመጣም ነው ያሉት፡፡ አምራቾች ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡበት የገበያ ማዕከል በ2012 ዓ.ም ቢገነባም ወደ ሥራ አለመግባቱን ነው ያነሱት። ማዕከሉ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል እና ማሽኖች ባለመሟላታቸው ምክንያት ነው ወደ ሥራ ያልገባው።
ሥራው የሚከናወነው በባሕላዊ መንገድ መኾኑም ተጽዕኖው ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። እስከ 700 ሜትር ርዝመት ቁፋሮ እና አፈር ማውጣት በሰው ኀይል የሚሠራ በመኾኑ ለአደጋ ያጋልጣል ነው ያሉት፡፡ ችግር ባለበትም ቢኾን በ2017 በጀት ዓመት በወረዳው 26 ሺህ ኪሎ ግራም ኦፓል ወደ ማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል። ከዚህም ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዝናው አበበ የክልሉን የማዕድን ሃብት ለመጠቀም ቢሮው በኢንቨስትመንት እና በጅኦ ሳይንስ ዘርፍ በጥናት ተደራጅቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የክልሉን የማዕድን ሃብት በራስ አቅም ለመጠቀም በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። በጥናቱ ካርታዎችን በማዘጋጀት የማዕድን ሃብት ያሉበትን ቦታዎች የመለየት ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል። የማምረት ሒደቱ ባሕላዊ በመኾኑ ወደ ውስጥ በሚቆፍሩበት ጊዜ የናዳ ጉዳት ይደርሳል ያሉት ኀላፊው ይህንን ችግር ለመፍታት በቴክኖሎጅ ለመደገፍ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
አምራቾች እና ላኪዎችን በቀጥታ ለማገናኘት በወረዳው የተገነባውን የገበያ ማዕከል ሥራ ለማስጀመር ማሽኖች በቢሮው መገዛታቸውን ተናግረዋል። የሰው ኀይሉን ለማሟላትም የአሠራር መመሪያ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። ኦፓልን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብም በአካባቢው የሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ሥልጠና እንዲሰጡ እና የገበያ ትስስር እንዲኖር በተያዘው በጀት ዓመት በትኩረት ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ 32 ሺህ 153 ኪሎ ግራም የጌጣ ጌጥ ማዕድን ተመርቷል። ከ9 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ወደ ውጭ በመላክ 9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleቡሄን በደብረ ታቦር
Next article“ስሙን የወረስሽ፣ ክብሩን የጠበቅሽ”