
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴት መገኛ ከኾኑ ከተሞች ውስጥ ደብረ ታቦር ከተማ አንዷ ናት።
በከተማዋ በየዓመቱ በክረምቱ ወራት በድምቀት ከሚከበሩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር (ቡሔ)፣ አሸንድዬ እና አድርሽኝ ተጠቃሾች ናቸው። ነሐሴ 13 የሚከበረው የደብረ ታቦር በዓል (ቡሄ) ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን እና ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ የርዕሰ አድባራት ደብረ ታቦር ኢየሱስ እና የመካነ ብርሃን ቅድስት ስላሴ አድባራት ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ቤዛ ዓለሙ እንደገለጹት የደብረ ታቦር በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ መለኮቱን ለሐዋሪያት እና ነብያት በደብረ ታቦር ተራራ የገለጠበት፣ ብርሃን የታየበት እና ድምጸ መለኮቱ የተሰማበት ነው። በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል።
“ቡሄ” ማለት የብርሃን መገለጫ ወይንም “ገላጣ” ማለት ሲኾን በሀገሪቱም ክረምቱ፣ ከጭጋጉ፣ ከደመናው አልፎ ብርሃን እና ወገግታ የሚታይበት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሳ እየተገረሙ እና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግዬት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተው እና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ ይህንንም ለማስታወስ “ቡሄ” ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ ይሰጣል። በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ የችቦ ማብራት ሥርዓትም ይከናወናል።
የሐዋርያት መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሦስቱ ተማሪዎቹ (ለጴጥሮስ፣ለያዕቆብ እና ለዮሐንስ) በደብረ ታቦር ተራራ ምሥጢረ መለኮቱን መግለጡን ለማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች “ስለ ደብረ ታቦር” እያሉ እህል ከአማኞች በመሠብሠብ እና ገንዘብ በማዋጣት ጠላ፣ ዳቦ፣ ቆሎ ያዘጋጃሉ። ያዘጋጁትንም የበዓሉ ዕለት ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያ ሊያስቀድሱ ለመጡት አማኞች ይጋብዛሉ፤ ቅኔ በመቀኜትም በዓሉን ያከብራሉ፡፡
በዓሉ በቡሄ ባሕላዊ ዜማዎች፣ በልጃገረዶች ጨዋታዎች እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችም ይደምቃል፡፡ በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘት ያለው፣ ምጣኔ ሃብታዊ አቅምን ለማጎልበትም የጎላ በመኾኑ በመጤ ባሕል እንዳይበረዝ ማኅበረሰቡ ብሎም ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል። በዓሉን አስመልክቶ አሚኮ ያነጋገራቸው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ አዲስ ፈንታዬ እንዳሉት በዓሉ ከመድረሱ በፊት አልባሳት ከማሟላት ጀምሮ የጅራፍ ዝግጅት ይደረጋል። የበዓሉ ቀን ወጣቶቹ “ቁንጮ” የሚባለውን የጸጉር ዓይነት በመቆረጥ፣ ነጭ አልባሳት እና ለምድ በመልበስ እና ጅራፍ በማጮህ ያከብራሉ።
በተለይም ደግሞ ወጣቶቹ ከዋዜማው ጀምሮ በየቤቱ ዜማዎችን እያዜሙ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላልፋሉ። በየሰፈሩ እየዞሩ ሙልሙል ዳቧቸውን ይገምጣሉ። ቡሄ ጨፍረው የተሰጣቸውን ገንዘብ ያጠራቅማሉ። በበዓሉ ዕለት ደግሞ በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ክንውኑ ከተካሄደ በኋላ ወደ ምሽት በጎዳና ላይ በባሕላዊ ጭፈራ እና በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራሉ። በዓሉ ሰላም እና አንድነትን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መኾኑንም ነግረውናል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አለበል ደመላሽ በከተማ አሥተዳደሩ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የቡሄ በዓል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል መልዕክት ነሐሴ 13 በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። በዋዜማው ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ የፓናል ውይይት ይካሄዳል፤ የጎዳና ላይ ትዕይንት እና ሌሎች በዓሉን የሚገልጹ ክዋኔዎችም ይካሄዳሉ። በዕለቱ ደግሞ በርዕሰ አድባራት ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በድምቀት የሚከበር ይኾናል። ወጣቶች እና ልጃገረዶች በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል። በዓሉ በዕደ ጥበብ ለተሠማሩ እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ምጣኔ ሃብት በማጠናከር በኩል ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!