የአርሶ አደሮችን ሕይወት እየቀየረ ያለው የፍራፍሬ ምርት

10
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ለማምረት ምቹ የአየር ንብረት፣ ለም አፈር እና የውኃ ሃብት የሚገኝበት ነው። በክልሉ ፍራፍሬ ከሚያመርቱ አካባቢዎች መካከል ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ተጠቃሽ ነው።
አቶ ጀማል አብዱ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በፍራፍሬ ማምረት ላይ የተሠማሩ አርሶ አደር ናቸው። ፍራፍሬ ማምረት ከጀመሩ ሦስት ዓመት ኾኗቸዋል። በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻሉ የፓፓያ ዝርያዎችን፣ ማንጎ እና ሙዝ እንደሚያመርቱ ነግረውናል። ያመረቱትን ምርት በመሸጥ በ2017 በጀት ዓመት 500 ሺህ ብር ማግኘታቸውንም ገልጸውልናል። የፍራፍሬ ምርት በየጊዜው ገቢ የሚያስገኝ በመኾኑ ከሰብል ምርት ጋር ሲነጻጸር አዋጭ ነው ብለዋል። የገበያ ትስስር ችግር ለሥራቸው ችግር እንደኾነ ተናግረዋል። አልፎ አልፎ ምርቶቻቸውን በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚሸጡም ጠቁመዋል።
ሌላው በፍራፍሬ ማምረት ላይ የተሠማራው ወጣት ኢብራሂም ሙሐመድ በማኔጅመንት ዲግሪ ምሩቅ ነው። በፍራፍሬ ማምረት ለአምስት ዓመታት ሢሠራ ቆይቷል። በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ፖፖያ፣ ማንጎ እና ሙዝ በማምረት የተሻለ ገቢ አግኝቶ ኑሮው መሻሻሉን ነግሮናል። በተጨማሪም ከቋሚ ፍራፍሬዎች ውስጥ ባለው ክፍት ቦታ ሽንኩርት እና ቲማቲም የመሳሰሉ አትክልቶችን እያመረተ ተጠቃሚ እንደኾነ ነው የገለጸው። የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤትም የሙያ እና የግብዓት ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው አንስቷል።
የቃሉ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ዘቢባ ሠይድ ለፍራፍሬ ልማት አምራች አርሶ አደሮች የአካባቢውን የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረጉ የተሻሻሉ ዝርያ ችግኞችን በመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች በማፍላት በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚቀርብላቸው ተናግረዋል። ችግኝ ከመትከል ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስም የድጋፍ እና ክትትል ሥራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በዚህ ክረምትም የተሻሻሉ ችግኞችን በማፍላት አሠራጭተናል ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አሳልፍ አሕመድ በዞኑ ከሰባት ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በፍራፍሬ ተሸፍኖ በመስኖ እና ከመስኖ ውጭ እየለማ መኾኑንም ገልጸዋል። የዞኑን የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረጉ የፍራፍሬ ችግኞችን በመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች በማፍላት ለፍራፍሬ አምራቾች እንደሚያዳርሱ ተናግረዋል። ምርታማነትን ለመጨመር ለአርሶ አደሮች ሥልጠና በመስጠት ሙያዊ እገዛ ይደረጋል ነው ያሉት። የፍራፍሬ በሽታ ሲከሰት ኬሚካል ርጭት እንዲያገኙ የማመቻቸት ሥራዎች እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
በተራራዎች እና በተፋሰሶች ላይ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል። የገበያ ችግሩን ለመፍታት ወሎ የአትክልት እና ፍራፍሬ ግብይት ማኅበር በአዲስ ተደራጅቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ከአርሶ አደሮች ምርት በመግዛት ለተጠቃሚዎች እና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲላክ እየተሠራ ነው ብለዋል። በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት ከ645 ሺህ ኩንታል በላይ የፍራፍሬ ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት የተፈጥሮ ጸጋ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። ጸጋውን ለመጠቀም ራሱን የቻለ በጀት በመመደብ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች አቅርቧል ብለዋል። ፍራፍሬን በኩታገጠም በማልማት ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ አቮካዶ ምርት ወደ ውጭ መላክ መጀመሩንም አንስተዋል። በተፋሰሶች እና በተጎዳ ሥነ ምህዳር ላይ የፍራፍሬ ልማት በማከናወን ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ዘርፍ እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበዓለ ደብረ ታቦር በአብነት ትምህርት ቤቶች
Next articleቡሄን በደብረ ታቦር