
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ነሐሴ 13 ይከበራል። በዓሉ በምዕመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በሚባል ባሕላዊ ትውፊት ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ደብረ ጽዮን ሰላም አርጊው ማርያም ቤተ ክርስትያን የመጽሐፍት ትርጓሜ መምህር አባ ሔኖክ አዳነ በዓለ ደብረ ታቦር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ ዓበይት በዓላት መካከል አንዱ እንደኾነ ይገልጻሉ።
በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ደብረ ታቦር በሚባል ተራራ ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብርሃን የታየበት እና ድምጸ መለኮቱ የተሰማበት ዕለትን በማሰብ የሚከበር መኾኑን አብራርተዋል።
ቦታውም ከገሊላ ባሕር ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ አሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ “ታቦር” የሚባል ተራራ እንደኾነ ገልጸዋል። ይህንን መነሻ በማድረግ ደብረ ታቦር የሚባለው የታቦር ተራራ ማለት እንደኾነ ያስረዳሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ኾኖ ሦስቱን ሐዋርያት ጴጥሮስን፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስን ይዞ እያስተማረ ምሥጢር የገለጠበት ሥፍራ ነው ይላሉ።
እንደ አባ ሔኖክ ገለጻ የአብነት ተማሪዎችም ዕለቱን ያስቡታል፤ ከመምህራቸው ጋር ኾነው በዓለ ደብረ ታቦርን በጉባኤ ቤቶች ያከብሩታል፡፡
“ደብረ ታቦር የአብነት ተማሪዎች በዓል ነው” የሚሉት መምህሩ ጉባኤ ቤቶች የደብረ ታቦር ተራራ ምሳሌ፣ መምህራን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንዲኹም ተማሪዎች ደግሞ የሐዋርያት ምሳሌ መኾናቸውን አብራርተዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግም የአብነት ተማሪዎች በጉባኤ ቤቶች ከጥንት ጀምሮ በድምቀት እንደሚያከብሩት ነው የገለጹት።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የአብነት ተማሪዎች በሰፊው ዝግጅት በማድረግ ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እኽል ከምዕመናን እየለመኑ ዝግጅቶችን በማካሄድ እንደሚያከብሩት ነው የገለጹት።
ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ድግስ ይዘጋጃል። ምዕመናንን ጋብዘው እየዘከሩ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር አንስተዋል፡፡ በአኹኑ ሰዓት ተማሪዎች ገንዘብ በማዋጣት እየገዙ እንደሚያከብሩት ነው ያመላከቱት።
በደብረ ጽዮን ሰላም አርጊው ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአብነት ተማሪ ኦዝያን ዓለሜ የደብረ ታቦር በዓል በአብነት ትምህርት ቤት ልክ እንደ ሰርግ ደምቆ እንደሚውል ይናገራል።
የበዓሉ አከባበር እንደየ አካባቢው ሁኔታ የሚለያይ ቢኾንም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ግን ተመሳሳይ መኾኑን ነው የሚገልጸው።
ተማሪ ኦዝያን እንደሚገልጸው የጥራጥሬ እኽል ተገዝቶ ንፍሮ ይቀቀላል፤ እንጀራ፣ ጠላና ሌሎችም ነገሮች ይገዛሉ። ከተማሪዎች መካከል የሚያስተባብር አለቃ ይመረጣል፤ ሌሎች አስተናጋጅ ተማሪዎችም ይመደባሉ።
በአለቃው አስተባባሪነት ኹሉም ዝግጅቶች ይዘጋጃሉ። በዕለቱ ምዕመናንም ከቅዳሴ መልስ ወደ ጉባኤ ቤቱ እንዲመጡ ጥሪ ይተላለፋል።
ምዕመናንም ወደ ጉባኤ ቤቱ መጥተው የተዘጋጀውን ድግስ ይጋበዛሉ። የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ መምህራን እንዲሁም ከሌላ ቦታ የመጡ እንግዶችም ካሉ በጉባኤ ቤቱ ይሰባሰባሉ።
ከዚህም በኋላ ተማሪዎች ያዘጋጁትን ድግስ “ስለ ደብረ ታቦር” እያሉ ለምዕመናን ይዘክራሉ።
ሌላኛው የአብነት ተማሪ ሶሎሞን ቢያልፈው ከድግሱ ዝክር በተጨማሪ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በማከናወን በዓሉ በድምቀት ተከብሮ እንደሚውል አንስቷል።
ለዕለቱ የተመረጠ መዝሙር ይዘመራል፣ ቅኔ ይዘረፋል፣ ወረብ የተባለው ሥርዓትም ይከናወናል ነው ያለው። በዋናነት እንደየ ጉባኤ ቤቱ የሚቀርበው ልዩ የሃይማኖታዊ ዝግጅት ይለያያል።
በአቋቋም ጉባኤ ቤቶች የአቋቋም ዝግጅት፣ በቅኔ ጉባኤ ቤቶች የቅኔ መቀኘት (ዘረፋ) ዝግጅት፣ በዝማሬ ጉባኤ ቤት የመዝሙር ዝግጅት በአመዛኙ ይቀርባል። በኹሉም ጉባኤ ቤቶች ግን ዕለቱን የተመለከተ የወረብ ዝግጅት እንደሚኖር ነው ተማሪዎቹ የገለጹት።
በመጨረሻም ጸሎት ይደረጋል። ለከርሞ ቢያደርሰኝ ቢያደርሳችሁ እየተባለ ሁሉም ተማሪ በትምህርቱ፣ በዓለማዊ ወይም በመንፈሳዊ ሕይወቱ ቢኾን የሚሉትን እየተመኙ ስለት ይሳላሉ። አባቶች ይመርቃሉ።
በዚህ መልኩ የደብረ ታቦር በዓል በአብነት ተማሪዎች ዘንድ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እየተከበረ ዛሬም ድረስ ዘልቋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!