
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን የመመርመር አቅሟን ለማሳደግ እየሠራች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እየሰጡ ባለው ማብራሪያ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ሲገባ ከነበራት ዜሮ የመመርመር አቅም ተነስታ 31 ላቦራቶሪዎች ተቋቁመው በቀን 8 ሺህ ሰዎችን መመርመር የምትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ በዚህ ሳምንት ተጨማሪ ሰባት ላቦራቶሪዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡና ሌሎችም እንደሚቀጥሉ ዶክተር ዐብይ አስታውቀዋል፡፡ እስከ መጪው ሐምሌ ድረስ በቀን 14 ሺህ ናሙናዎችን የመመርመር አቅም ላይ እንደሚደረስም ነው ያስታወቁት፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ብዙ ሰዎችን በመመርመር ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋናና ሞሮኮ በመቀጠል በአራተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘‘ካለን ሕዝብ አንጻር ግን በቂ አይደለም’’ ብለዋል፡፡ መንግሥት ካለው መጠነኛ ሀብት 5 ቢሊዮን ብር መድቦ፣ ከወዳጅ ሀገራት የሚገኝን ዕርዳታ ጨምሮና ተጨማሪ ሀብት እየፈለገ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ጥሩ የኮሮና መከላከል ምሳሌ የሚሆን አመራር መስጠት መቻሉንም አብራርተዋል፡፡
በኮሮና ዙሪያ በባህላዊም ሆነ በሳይንሳዊ መንገድ የሚመጡ መፍትሔዎችን ጎን ለጎን በመውሰድ እየተመራ ያለበት አግባብም ጥሩ ተሞክሮ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እስከ 17 ሺህ 500 ሰዎችን ማከም የሚያስችሉ፣ 30 ሺህ የሚደርሱ ምልክት ያለባቸው ሰዎችን ለይቶ ማቆየት የሚችል እና 45 ሺህ ሰዎችን ከውጭ ሲገቡ ለማቆየት የሚችል ቦታ በመንግሥት ጥረት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡ ‘‘ይህ ግን የሚያኩራራ አይደለም፤ ለከባዱ ሁኔታ መዘጋጀት ያስፈልጋል፤ ይህንን ጥንካሬ ግን ወባ፣ ካንሰር፣ ኩፍኝና ሌሎችም በሽታዎች ላይ መድገም አለብን’’ ብለዋል ዶክተር ዐብይ፡፡ ይህ ሲሆን የብዙ ሰዎችን ሕይወት መታደግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡
‘‘ከመካከለኛው ምሥራቅና ከጎረቤት ሀገራት ዜጎቻችን ተገፍተው ሲመጡ መርምረን ጤንነታቸውን አረጋግጠን ተቀብለናል፤ ይህ በሌሎች ሀገራት ያልተለመደ ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት ዜጎች በራሳቸው ወጭ በቤታቸው እንዲነጠሉ ነው የሚደረገው፤ ኢትዮጵያ ግን አብልታ፣ አጠጥታ፣ ጤንነታቸውን አረጋግጣ መቀበሏ ዜጋ ተኮር ሥራችንን የሚያሳይ መልካም ጅማሮ ነው’’ ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ላቦራቶሪ እንደተገነባ ያመለከቱት ዶክተር ዐብይ ለሥራውም ‘‘ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፤ ከአንድ ቢሊዮን ብር ያላነሰ የቁሳቁስና የብር ድጋፍም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር መሠረት እንዲያገኙ ተደርጓል’’ ብለዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴርና የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኮሮናን በተመለከተ የሚታወቀውን መረጃ በሙሉ ለሕዝብ እያስታወቁ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ መረጃ መከልከል በሽታውን ከቁጥጥር ውጭ ሊያደርግ ስለሚችል የሚንስትሮች ኮሚቴ በወሰነው መሠረት በበቂ መረጃ በየጊዜው እየተሰጠስመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡
በአብርሃም በዕውቀት