
ጎንደር፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2018 የትምህርት ዘመን የተሻለ የመማር ማስተማር ለማካሄድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል።
”አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታ ውጭ አይኾንም” በሚል መሪ መልዕክት የ2018 ዓ.ም የትምህርት ምዝገባ እና የትምህርት ቤቶች ምገባ መርሐ ግብር የንቅናቄ መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ ግብዓት እና የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት ለመማር ማስተማሩ ሥራ እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።
የኮምፒውተር፣ የማጣቀሻ መጽሐፍት እጥረት እና የትምህርት ቤቶች ደረጃ ዝቅተኛ መኾን ለመማር ማስተማር ሥራው ችግር መፍጠራቸው ተጠቅሷል።
በ2017 በጀት ዓመት ሁለት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የጠቀሱት ኀላፊው በቀጣይ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር የተጠናከረ ሥራ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ የትምህርቱን ዘርፍ ለመደገፍ ከተለያዩ አካላት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ በመሠብሠብ እና ከከተማ አሥተዳደሩ ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ያለፈው ዓመት በሰላም እጦቱ ምክንያት በከተማ አሥተዳደሩ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑበት እና የተወሰኑ የትምህርት ተቋማትም አገልግሎት ያልሰጡበት ዓመት እንደነበር ጠቅሰዋል።
የትምህርት ስብራት ትውልዱን የሚጎዳ በመኾኑ ችግሩ እንዳይደገም ከተማ አሥተዳደሩ እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ወደፊት ለውጥ የሚያመጣ ተግባር መከወን አለባቸው ብለዋል።
ዘጋቢ :-ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!