
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2018 ዓ.ም አንድም እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾን እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
ቀጣይነት ያለው የተማረ፣ የሰለጠነ እና የተለወጠ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ትምህርት ላይ መሥራት ብቸኛው አማራጭ ነው።
በውስጥም በውጭም ባሉ ግጭት ጠማቂዎች መመሪያ ሰጭነት በክልሉ ሁለት ዓመት የሞላው ግጭት ትምህርት ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ማለፉን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በውጤቱም ትምህርት ቤቶች ጉዳት አስተናግደዋል፤ ከፖለቲካ ነጻ የኾኑ መምህራን ሥራ አጥ ከመኾን ባሻገር ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሕይዎታቸውን አጥተዋል፤ ህጻናት ተማሪዎች ቤት እንዲውሉ እና አልባሌ ቦታ እንዲውሉ ኾነዋል፤ ወላጅ ቤተሰብ እጅጉን አዝነው በየመድረኩ በድፍረት እና በምሬት ገልፀዋል ነው ያሉት።
ይህ አስከፊ ሁኔታ እንዲለወጥ በተከፈለው መራር ተጋድሎ ተማሪዎቻችን ወደ ትምህርት ቤት የመመለስ እና ትምህርት ቤቶችን ምቹ የመማሪያ ቦታ ለማድረግ አበረታች ውጤት መገኘቱንም ጠቁመዋል።
በ2018 ዓ.ም አንድም እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾን እየተሠራ መኾኑንም ገልፀዋል።
ዛሬ በተመረጡ አካባቢዎች ተማሪ የመመዝገቡ ሥራ በአንድ ጀምበር በርካታ ተማሪዎችን በመመዝገብ የ2018 የመማር ማስተማሩ ምዝገባ ሥራ በይፋ ተጀምሯል ነው ያሉት።
በክልላችን ከተማሪዎች ምዝገባ ጀምሮ በተሟላ ደረጃ የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና ወጣቶች የትውልድ ግንባታ ሥራ ነውና የያዝነው ተግባር ታሪካዊ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!