
ደብረታቦር፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረታቦርን በደብረታቦር በዓል የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለበል ደመላሽ የበጌምድሯ ፈርጥ ደብረታቦር ከተማ ታሪክ፣ ተፈጥሮ፣ ዕምነት እና ባሕል ተባብረው የሚያደምቋት ከተማ ናት፤ የዚህ ድምቀትም አንዱ ደብረታቦርን በደብረታቦር (ቡሔ) በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ ትውፊቱን በጠበቀ ውብ የቡሔ ጭፈራ፣ ልብ በሚከፍት የጅራፍ ጩኸት፣ ብርሃንን በሚገልጥ ችቦ፣ ነጭ በነጭ ተወቦ በሚታይ ባሕላዊ አለባበስ፣ መንፈስን በሚያድስ የተክሌ ዝማሜ፣ በእንግዳ ተቀባይነት ዝክር እና በሙልሙል ዳቦ የበረከት ስጦታ ታጅቦ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቱን ጠብቆ በድምቀት መከበሩ ልዩ ትርጉም ያለው መኾኑን ያሳያል ነው ያሉት።
የጥቁር ሕዝቦች ድል የኾነውን ዓድዋን ስናስብ አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ግንባር ቀደም ናቸው ያሉት ኀላፊው በቡሔ ዋዜማ ልደታቸው መኾኑ በዓሉን የተለየ ድምቀት ሰጥቶታል ብለዋል።
ባሕሉ ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ በባሕሉ እና በማንነቱ የሚኮራ ማኅበረሰብ መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን
ነሐሴ ወር ለደብረታቦር ከተማ ድርብ መልክ እና ገጽታ አለው ብለዋል።
አካባቢው በቱሪዝም ዘርፍ ብዙ ዕድሎች እንዳሉት ያነሱት ከንቲባው ይህንንም ጥናት በማድረግ በመለየት እና ተቀናጅቶ በመሥራት ማኅበረሰቡን መጥቀም እንዲችል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ታሪክ እና ባሕልን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ የአማራ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የሚታደሙባቸው በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት የሚከበሩበት መኾኑን ገልጸዋል።
ዘመን ሲቀየር ዘመን የማይሽራቸው፣ ሲከወኑ ታዳሚ የማይሰለቻቸው፣ ትውልድ ሁሉ በቅብብሎሽ የሚያከብራቸው፣ ታሪክን ከማንነት፣ ጥበብን ከባሕል፣ ትውፊትን ከታሪክ ጋር አስተሳስረው የሚከበሩ በዓላት ባለቤቶች በመኾናችን ልንኮራባቸው እና ልንጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት።
ውብ እና ባሕላዊ እሴቶችን ታሪክ ተናጋሪ ከኾኑት ቅርሶች እና የመስህብ ቦታዎች ጋር በማጣመር የቱሪዝም ዘርፉን አገልግሎት በማሳለጥ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!