ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

9

ከሚሴ፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አርጡማ ፉርሲ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎችን የሚያገናኝ የማሽላ ኩታገጠም ሰብል ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚገኙ የወረዳ የከተማ አሥተዳደር እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የወረዳዎች የግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች በወረዳው የተመለከቱት የማሽላ ኩታገጠም ሰብል እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። አርሶአደሮች የተሟላ ሥራ በመሥራታቸውን የተሻለ የሰብል ቁመና እንዲያዩ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።

የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኪሶ ከፋለ የማሽላ ኩታገጠሙ የዲምቱ ጨቆርሶ እና ወገሬ ደበሶ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ መኾኑን ጠቅሰዋል። ሰብሉ ከ700 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚሸፍንም አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሀሰን ሰይድ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ58ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር ሰብል መሸፈኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ ውስጥ ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ የሚኾነው መሬት በመደበኛ ኩታገጠም መሸፈኑን አስረድተዋል።

ሰፋፊ የኩታገጠም እርሻዎችን ለመፍጠርም በተደረገው ጥረት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ11 በላይ ሰፋፊ የኩታገጠም እርሻዎች በሰብል መሸፈን ተችሏል ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰፋፊ ኩታገጠሞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

አርሶአደሮች በመስመር በመዝራት የተሟላ ግብርና እንዲጠቀሙ በመደረጉ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምርታማነት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም ገልጸዋል።

በቀጣይ ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኝ ሰፋፊ የኩታገጠም እርሻ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወረርሽኞችን በቅንጅት መከላከል ተችሏል።
Next articleነሐሴ ወር ለደብረታቦር ከተማ ድርብ መልክ እና ገጽታ አለው።