ወረርሽኞችን በቅንጅት መከላከል ተችሏል።

10

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጤና ችግሮች እና የትግበራ ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ ግምገማዊ ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ እየሰጠ ነው።

የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ተከስተው የነበሩ የወረርሽኝ አይነቶችን በቅንጅት በመሥራት መከላከል መቻሉን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በርካታ ወረርሽኞች ነበሩ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ኮሌራ፣ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ)፣ ወባ፣ ኩፍኝ እና መሰል በሽታዎችን በዋናነት ጠቅሰዋል።

እነዚህን የበሽታ አይነቶች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት በክትባት መከላከል መቻሉን ነው የተናገሩት።

በ2016 ዓ.ም እና በ2017 ዓ.ም ተከስቶ የነበረውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል ከ5 ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች ምርመራ መደረጉን አንስተዋል።

ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ሰዎች በወባ በሽታ ተጠቅተው በመገኘታቸውም ሕክምና እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል።

በቅንጅት በመሠራቱም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በከፍተኛ ኹኔታ መቀነስ መቻሉን ነው ያብራሩት።

በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የኤም_ፖክስ በሽታም ፈጥኖ ምላሽ በመሰጠቱ በሽታው አድማሱን ሳያሰፋ መከላከል መቻሉን ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከወረርሽኝ ባሻገር በሌሎች የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ክስተቶች ሲደርሱም የነፍስ አድን ሥራ ያከናውናል ብለዋል።

በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ.ር) ክልሉ በገጠመው የግጭት ዓውድ ውስጥ የጤና ሥርዓቱን ለመደገፍ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ሥራዎች ማከናዎናቸውን ተናግረዋል።

የተለያዩ ወረርሽኞች ሲከሰቱም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እየተጫዎቱ ይገኛሉ ብለዋል።

በባለፉት ዓመታት ክልሉን የፈተኑት ወባ እና ኮሌራን ለመከላከል ዩኒቨርሲቲዎች የተጫወቱት ሚና ቀላል የማይባል መኾኑን ነው የተናገሩት።

በአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ባለሙያ ጥሩነህ ገነቱ እንዳሉት ከፍተኛ የሚባሉ የኀብረተሰብ የጤና አደጋዎችን በቅንጅት በመሥራት አደጋዎች የስርጭት አድማሳቸውን ሳያሰፉ የጉዳት መጠናቸውን በመቀነስ መቆጣጠር ተችሏል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የአማራ ክልል ተወካይ የሌና ማድራቪች ተቋማቸው በክልሉ ውስጥ ጤና እና ጤና ነክ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት እና ከደረሱ በኋላ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።

ሌሎች የሰብዓዊ ተቋማትም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲሰጡ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሠራ ነው የገለጹት።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአሚኮ ቀዳሚ ኾኖ በብሔረሰቦች ቋንቋ መሥራቱ ረጅም ራዕይ ያለው መኾኑን ያመላክታል። 
Next articleምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።