አሚኮ ቀዳሚ ኾኖ በብሔረሰቦች ቋንቋ መሥራቱ ረጅም ራዕይ ያለው መኾኑን ያመላክታል። 

24

ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ከተመሠረተበት 1987 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሚዲየሞች የቋንቋ፣ የዓየር ጊዜ እና የተደራሽነት ሽፋኑን በማሳደግ እያገለገለ ያለ የሕዝብ ሃብት ነው።

በ”በኩር” ጋዜጣ የተጀመረው አገልግሎት በ30 ዓመታት ጉዞው በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ፣ በኤፍ ኤም፣ በጋዜጣ እና በዲጂታል ሚዲያ አድማሱን ያሰፋ ግዙፍ ሚዲያ ኾኗል።

አሁን ላይ ሁለት የውጭ ቋንቋዎችን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋን የሚሰጠው አሚኮ ለክልሉ ብሔረሰቦችም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።

ለኽምጣና፣ ለአዊኛ እና ለኦሮሞ ብሔረሰብ ቋንቋዎችም የቴሌቪዥን፣ የሬድዮ፣ የጋዜጣ እና የዲጂታል ሚዲያ ሽፋን በመስጠት መረጃ በሰፊው እያደረሰ ይገኛል።

ለብሔረሰቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚዲያ ሽፋን መስጠት ሰብዓዊ ብዝኃነትን ከማክበርም በላይ በሀገራቸው ምጣኔ ሃብት እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ ማድረግ ነው።

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የኽምጣና ዜና እና ፕሮግራሞች ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ወንድሙ ቸኮለ አሚኮ በአማራ ክልል ውስጥ በሚነገሩ የብሔረሰብ ቋንቋዎች ስርጭት ማድረጉ የክልሉን ገጽታ ለማስተዋወቅ እና የብሔረሰቦችን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ መስጠት ያስቻለ ነው ብለዋል።

አሚኮ በጋዜጣ፣ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን እና በዲጂታል ሚዲያ ዜና እና ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ቋንቋውን የመጠቀም፣ የማሳደግ እና ሃሳቡን የመግለጽ መብቱን እንዲተገብር እያገዘ መኾኑንም አንስተዋል።

እኛ የዋግ ሕዝብን ቋንቋ፣ ባሕል፣ ትውፊት፣ ታሪክ በአጠቃላይ ማንነቱን ለመግለጽ በሚዲያው ስንሠራ ቋንቋውን የሚናገሩ፣ የሚያዳምጡ እና የሚያነቡ ሰዎች ግብዓቶች እየሰጡን ነው። ለዚህም የአሚኮ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አሚኮ ከክልል ሚዲያዎች ቀዳሚ ኾኖ በብሔረሰቦች ቋንቋ መሥራቱ ረጅም ራዕይ ያለው መኾኑን ያመላክታል ነው ያሉት። ሁሉም የክልሉ ሕዝብ በሚዲያው የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው አድርጓል ብለዋል።

ሻደይን ጨምሮ የተለያዩ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብን የሚያስተዋውቁ ፕሮግራሞችን ሢሠራ መቆየቱን ያስታወሱት ጋዜጠኛ ወንድሙ ሕዝባዊ በዓላትን፣ ታሪክን እና ባሕልን በቋንቋው በማክበር ለዋግ ሕዝብ ማንነት መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ገልጸዋል።

በብሔረሰብ ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋን የሚሰጥበት የአየር ጊዜው እያደገ መኾኑንም አንስተዋል። የሰቆጣ ኤፍ ኤም ግንባታ ተጠናቅቆ ቁሳቁስ መሟላት ብቻ እንደቀረው የተናገሩት ጋዜጠኛ ወንድሙ በቅርቡ ሥራ ሲጀምርም የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ሕዝብ በኽምጣና ቋንቋ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የኦሮምኛ ዜና እና ፕሮግራሞች ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬዘር አድማስ ቋንቋ ለአንድ ማኅበረሰብ ባሕል ማደግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ቋንቋው በሚዲያ ሥራ ላይ ሲውል ማኅበረሰቡ ራሱን ለመግለጽ፣ ባሕሉን ለማዳበር እና ለማጉላት ትልቅ መሣሪያ እንደኾነ ነው የገለጹት።

አሚኮ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚዲያ ሽፋን መስጠቱ ሰዎች ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውን እና ማንነታቸውን እንዲያዳብሩ ዕድል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። አሚኮ ለክልሉ ብሔረሰቦች ማንነት መጎልበት እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ቋንቋ ባሕልን፣ ማንነትን እና ታሪክን የመሰሉ እሴቶችን ያቀፈ በመኾኑ ለአንድ ማኅበሰረብ መሠረታዊ እንደኾነ ነው የገለጹት። የሥልጣኔ መነሻ እና ማስተላለፊያም ነው ብለዋል። አሚኮም ብሔረሰቦች ይህንን ሃብት እንዲያዳብሩት እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በአፋን ኦሮሞ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች በክልሉ ውስጥ ብቻ ሳይኾን ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ ሕዝቦችም ትክክለኛውን መረጃ በማሳወቅ ወንድማማችነት እና አንድነት እንዲፈጠር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበራዊ ትስስርን፣ የጋራ ታሪክ እና እሴትን በመግለጽ ከክልሉም አልፎ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አሚኮ በትጋት እየሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

አሚኮ በብሔረሰብ ቋንቋዎች ዜና፣ ፕሮግራሞች፣ ማስታወቂያ፣ መዝናኛ እና ሌሎችንም ሲያሰራጭ በቋንቋው እና በባሕሉ ተመስርቶ በመኾኑ የብሔረሰቡ ሁለንተናዊ እድገት እንደሚፋጠን አንስተዋል።

በሙሉዓለም ባሕል ማዕከል የኪነ ጥበብ ባለሙያ ተዋናይ ደሳለኝ መኩሪያው አሚኮ የብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋዎች በማካተት ስለሚሠራ ልሣናችን ነው ብለዋል።

አንድ ቋንቋ የሚያድገው በሥነ ጽሑፍ ሲጻፍ፣ በኪነ ጥበብ ሲከተብ እና የሚዲያ ቋንቋም ሲኾን ነው ያሉት ተዋናዩ አሚኮ የአዊኛ ፕሮግራም ከጀመረ በኋላ በአዊ ብሔረሰብ ሕዝብ እና ተወላጅ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል። በመጀመሪያ አገውኛ ቋንቋን በሬድዮ መስማት ለብዙ ሰዎች ሀሴትን የፈጠረ ነበር፤ ቀጥሎም በሳምንት አንዴ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መጀመሩም ሌላ ደስታን የፈጠረ እንደነበር አስታውሰዋል። ለቋንቋው እድገትም ትልቅ አቅም መኾኑን ተናግረዋል።

አዊኛ ቋንቋ በአሚኮ መካተቱ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በመሥራት ቋንቋውን ለመጠበቅ እና ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። ቋንቋውን እየሰሙ መናገር ለማይችሉ ብዙ ሰዎችም ቋንቋውን መናገር እንዳስቻላቸው ነው አርቲስት ደሳለኝ የገለጹት። አሚኮ ለተለያዩ ቋንቋዎች ትኩረት በመስጠት ሽፋን መስጠቱ የሚያበረታታ፣ መነሣሣትን የፈጠረ እና ለእድገቱም መሠረት ነው ብለዋል።

ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሙያቸውን እንዲተገብሩ እና እንዲያስተዋውቁ በማድረግ አሚኮ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል። የኪነ ጥበብ ሥራዎች በተለይም ሙዚቃዎች በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ሲቀርቡ ቋንቋውንም ባለሙያውንም ለሕዝብ ተደራሽ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት። ባለሙያውም ወደ ሕዝብ እንዲደርስ አንድ አማራጭ ኾኖ ማገልገሉን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ አንታጉ በተሰኘ የአገውኛ ፊልም ላይ መሳተፋቸውን የገለጹት ተዋናይ ደሳለኝ ይህም ኪነ ጥበቡ ለሕዝብ መድረሻ ሚዲያ እንዳለው በመተማመን የተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል። አሚኮ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሀሳባችን የምንሸጥበት ሚዲያ ነው፤ ለረጅም ዓመታት በየቋንቋችን ሥራችንን ለማኅበረሰቡ አድርሰንበታልም ብለዋል።

በአሚኮ ለቋንቋዎች የሚሰጠው የአየር ሰዓት እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት ተዋናይ ደሳለኝ ብሔረሰቦቹ ካላቸው ሰፊ የባሕል እሴት አኳያ በቀጣይም የአየር ሰዓት እና የዘጋቢዎች ቁጥርን በመጨመር ለቋንቋዎች ማደግ እና ለብሔረሰብ ሕዝቡ ባሕል ማደግ እና መስፋፋት የበለጠ እንዲሠራም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ: ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበጤናው ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶችን መሰነድ ፋይዳው ከታሪክ በላይ ነው።
Next articleወረርሽኞችን በቅንጅት መከላከል ተችሏል።