የኢትዮጵያ ዓመታዊ ዕድገት ከ170 በላይ ሀገራት በተሻለ ስድስት በመቶ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ፡፡

199

የባንኮች የብድር ብልሽት መቀነሱንና ቁጠባ ማደጉንም ተናግረዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ በተያዘው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ዓመታዊ ዕድገት ከታቀደው 9 በመቶ ባነሰ 6 በመቶ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ይህም ‘‘ከ170 በላይ ሀገራት ከዜሮ በታች ዕድገት በሚያስመዘግቡበት ወቅት ይህ ዕድገት ከፍተኛ ነው’’ ብለዋል፡፡ የዓለም የገንዘብ ተቋም ትንበያ ግን የኢትዮጵያ ዕድገት 3 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ማመላከቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ መንግሥት በኮሮና ቀውስ ወቅት ምጣኔ ሀብቱን በጥንቃቄ ለመምራት መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የበጀት ዓመት ከሐምሌ መጀመሩና እስከ መጋቢት በጥሩ የዕድገት ደረጃ መቀጠሉ፣ የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የንግድ ትስስር ከ30 በመቶ በታች መሆን፣ ኢትዮጵያ ከ5 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኪሳራ በገጠመው የአክሲዮን ገበያ (ስቶክ ማርኬት) አለመግባት ምጣኔ ሀብቷ ላይ ክፉኛ ጉዳት እንዳይገጥማት ማድረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት የካፒታል አካውንት ክፍት ባለመሆኑ የዓለም ኢኮኖሚ ሲናጋና ሲዘጋ አለመጎዳቱንም አመልክተዋል፡፡

ባንኮች ባለፉት 10 ወራት 87 ቢሊዮን ብር ቁጠባ መሰብሰባቸውንና ይህም ካለፈው ዓመት 17 ከመቶ ቁጠባ ማደጉን እንደሚያሳይ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ለኢንቨስትመንት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑንና የተመለሱ ብድሮችም 14 ከመቶ ማደጉን ዶክተር ዐብይ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተያዘው በጀት ዓመት 221 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱንና 24 ከመቶ ማደጉንም ተናግረዋል፡፡ የተበላሸ ብድር በዘንድሮው በግል ባንኮች 3 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን፣ ከአምናው ጋር ሲነጻጸርም በ4 በመቶ መቀነሱን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበላሸ ብድር 2 ከመቶ እንደሆነና ባለፉት አስር ወራት 43 ከመቶ የተበላሸ ብድር መስተካከሉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡ ከፍተኛ የብድር ብልሽት ያለበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብልሽቱ34 ከመቶ እንደሆነ ተመላክቷል፤ ያም ሆኖ ግን ከባለፈው ዓመት በ13 መቶ እንደቀነሰ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ከግል ባንኮች ቦንድ ማስቀረቱ፣ ለንግድ ባንኮች ከኮሮና ጋር በተያያዘ48 ቢሊዮን ብር ብሔራዊ ባንክ ፈሰስ ማድረጉ፣ አነስኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች እንዳይጎዱና ብድር እንዳይጓጎል መደረጉ፣ ከፍተኛ ዕዳ ለነበረባቸው ግብር ከፋዮች ከ78 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ምሕረት መደረጉ ምጣኔ ሀብቱን መታደጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮቹ አብራርተዋል፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
Next articleበኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አቅምን በቀን ከ14 ሺህ በላይ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ፡፡