በጤናው ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶችን መሰነድ ፋይዳው ከታሪክ በላይ ነው።

11

ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጤና ችግር ምላሽ አሰጣጥ ሰነድ ዙሪያ ግምገማዊ ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው።

በሥልጣናው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ባለፉት አምሥት ዓመታት ገደማ በክልሉ የተወሳሰበ የጤና ችግር ማጋጠሙን አስታውሰዋል። ችግሮች እየተገመገሙም አፋጣኝ ምላሽ መሰጠቱንም ተናግረዋል።በሥራው ሂደት የተገኙ ውጤቶችን፣ ተሞክሮዎችን እና ችግሮችን የመሰነድ ሥራም ተከናውኗል ነው ያሉት። ሰነዱ ለሀገር ውስጥ ተመራማሪዎች የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች ታትመው የዓለም ማኀበረሰብ በመረጃ ላይ ተመርኩዞ ሃብት እና ግብዓት እንዲደግፍ አይነተኛ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።

የሰሜኑ ጦርነት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና አሁን ያለው የጸጥታ ችግር ተደምሮ የጤና አደጋዎችን ምላሽ አሰጣጥ የከፋ አድርጎት መቆየቱን ተናግረዋል። በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የደረሰው የጤና ጉዳት እንደ ክልል ተጠንቷል ያሉት ዳይሬክተሩ በመጽሐፍ እና በምርምር መጽሔቶችም እንዲወጣ መደረጉን ጠቁመዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠረው ግጭት በክልሉ የወደመው የጤና ጉዳት በጥናት መለየቱን ተናግረዋል። ይህም በርካታ ጥቅም ያስገኛል ነው ያሉት። በክልሉ የገጠመውን የተወሳሰበ የጤና ችግር ምላሽ ለመስጠት በሀገራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅንጅት እየተሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ያለፈውን የሁነት ሰነድ ሰንዶ መያዝ ጥቅሙ ከታሪክ በላይ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ሰነዱ ከኀብረተሰብ ጤና አንጻር ለክልሉ መንግሥት ፖሊሲ እና ስትራቴጅ ቅመራም ከፍተኛ ፋይዳ አለው ነው ያሉት። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የአማራ ክልል ተወካይ የሌና ማድራቪች “በክልሉ የሚገጥሙትን የኀብረተሰብ አዳጋዎች ዘርፈ ብዙ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ብለዋል። ሌሎች ረጂዎችም በጤናው ዘርፍ እንዲረዱ ተዓማኒ መረጃዎች አስፈላጊ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየዚገም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ወደ መጠናቀቅ መቃረቡ ተገለጸ።
Next articleአሚኮ ቀዳሚ ኾኖ በብሔረሰቦች ቋንቋ መሥራቱ ረጅም ራዕይ ያለው መኾኑን ያመላክታል።