
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዚገም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ወደ መጠናቀቅ መቃረቡን የወረዳው አሥተዳደር አስታውቋል።
በ2011 ዓ.ም ተጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከአምስት ዓመት በላይ ተቋርጦ የቆየው የሆስፒታሉ ግንባታ በ2016 ዓ.ም በመቅደላ ኮንስትራክሽን አማካይነት እንደገና ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁ ተገልጿል። በወረዳው የአካባቢ ሆስፒታል ባለመኖሩ ምክንያት ታካሚዎች ለሕክምና ከ45 እስከ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ወዳሉ ሆስፒታሎች ለመሄድ ይገደዱ ነበር። በዚህም ምክንያት ሊድኑ ይችሉ የነበሩ በርካታ እናቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ሌሎች ታካሚዎች መንገድ ላይ ሕይዎታቸውን እንዳጡ ነዋሪዎች እና አሥተዳደሩ ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጅ ባዘዘው የኔሰው እንዳሉት የቀድሞው የግንባታ ሂደት ከ54 በመቶ አይበልጥም ነበር። አሁን ላይ ዋና ዋናዎቹ ሥራዎች ተጠናቅቀው የቀሩት የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ ናቸው። ኾኖም በክልሉ የነበረው የሰላም ችግር እና አንዳንድ የግንባታ እቃዎች እጥረት ሥራውን በተወሰነ መልኩ ማዘግየቱን ተናግረዋል። የዚገም ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መልካሙ አለነ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ የወረዳው ትልቁ የልማት ፕሮጀክት መኾኑን ገልጸው በ2018 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ግንባታው እዚህ ደረጃ የደረሰው የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የክልሉ መንግሥት እና የዞኑ አሥተዳደር ባደረጉት አስተዋጽኦ መኾኑንም አክለዋል።
የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የጤና ሚኒስቴር እና የጤና ቢሮ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የወረዳው አሥተዳደር ጥሪ አቅርቧል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አህመድ ሁሴን ለሆስፒታሉ አገልግሎት የሚያገለግል አንድ አምቡላንስ መዘጋጀቱን እና የሰው ኀይል እና የቁሳቁስ አቅርቦት ሥራዎች በሂደት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!