
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለፉት 30 ዓመታት በማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዘርፈ ብዙ የሚዲያ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በጤናው ዘርፍም የማኅበረሰቡ ጤና እንዲሻሻል በኹሉም የሚዲያ አማራጮች የጤና መረጃዎችን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ እዚህ ደርሷል።የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ቢሮው የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ እንዲያከናውናቸው በሕግ የተሰጡትን ተግባራት ለመፈጸም አሚኮ ድልድይ በመኾን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።ቢሮው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርገው በአሚኮ አማካኝነት መኾኑንም አንስተዋል። ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የአሚኮ ድርሻ ትልቅ ነው ብለዋል።
አሚኮ በቀበሌዎች እና ወረዳዎች ፈጥኖ በመድረስ እና ትክክለኛውን መረጃ ለሕዝብ በማድረስ ለጤናው ዘርፍ አስተዋጽኦ ያበረከተ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል። በጤናው ዘርፍ የማኀበረሰቡ ንቃተ ኅሊና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ አሚኮ የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል ነው ያሉት። አሚኮ ለጤና ዘርፍ የጀርባ አጥንት የኾነ ተቋም ነው ብለዋል። ጤና ቢሮው እስከ አኹን ድረስ ከአሚኮ ጋር በነበረው የሥራ ግንኙነት ደስተኛ እንደኾነ የገለጹት ምክትል ኀላፊው በቀጣይም ግንኙነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አንሻ መሐመድ አሚኮ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የጤና መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል። ከዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ጋር ተናቦ በመሥራት በጤና ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን የዘገባ ሽፋን እንዲያገኙ አድርጓል ነው ያሉት። ወቅታዊ እና ትክክለኛ የጤና መረጃዎችን ለማኅበረሰቡ በማድረስ በኩል አሚኮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!