
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጾመ ፍልሰታ በወርሐ ነሐሴ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ለ15 ቀናት የሚትጾም ጾም ናት።
በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ከሚጾሙት ሰባት አጽዋማትም አንዷ ናት። በዚህ የጾም ወቅት ምዕመናን አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጾም እና በጸሎት ያሳልፋሉ። ከተለመደው ጊዜም ወጣ ባለ መልኩ ሃይማኖታዊ ትምህርት እና ጸሎት በቀን ውስጥ ሰፊውን ጊዜ ይይዛሉ። ታዲያ በዚህ የጾም ጊዜ ምዕመናን ራሳቸውን ገዝተው ለመልካም ሥራ ይተጋሉ፤ ካላቸው ቀንሰው ለተቸገሩት ይረዳሉ፤ እርስ በእርስ መተጋገዝን እና መደጋገፍንም ያጠናክራሉ። ይህ ደግሞ ለሰላማዊ ሕይዎት መሠረት የሚጥል ነው። እንደ ሕዝብ አካባቢያዊ እና ሀገራዊ ሰላም እንዲኖር ሚናውም ከፍተኛ ነው።
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ገዳመ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እና የትርጓሜ መጽሐፍ መምህር የኾኑት መምህር ዘላለም በላይ ስለ ጾመ ፍልሰታ ሲያስረዱ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሉት አጽዋማት አንዷ እንደኾነች ገልጸዋል። የጾመ ፍልሰታ ከድንግል ማርያም የዕረፍት እና ዕርገት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡ በቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ መሠረት ጾም ማለት መከልከል ሲኾን ምዕመናን ከስጋዊ ፍላጎት እና ድሎት የሚከለከሉበት እና ለነፍሳቸው የሚኾን ስንቅን ማለትም ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት እና ምጽዋትን በትኩረት የሚተገብሩበት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ጾም ምዕመናን የድንግል ማርያምን ዕርገት እያሰቡ ይጾማሉ፤ ሌሎች ክርስቲያናዊ ግዴታዎችንም ይወጣሉ ነው ያሉት፡፡
በዚህ ጾም ምዕመናን በቅን ልቦና ለወገኖቻቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገራቸው እንዲሁም ለፍጥረት ሁሉ በጎ የሚያስቡበት፣ የሚጸልዩበት ወቅት እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ፍልሰታ በተለይም ደግሞ ሕጻናት ሳይቀሩ ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ የሚጾሙባት እና ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን የሚፈጽሙበት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ጾም ሁሉም ምዕመናን ጾታ፣ እድሜ እና ሌሎች ሁኔታዎች ሳይበግራቸው ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው የሚያስገዙበት ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች በፍልሰታ ጾም አብዛኛውን ጊዜያቸውን በቤተ ክርስቲያን እና መልካም ሥራ በመሥራት ያሳልፋሉ፡፡ ይህም አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ፤ በሕይዎታቸው መሠረት እንዲይዙ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ሁሌም ስለ ሀገር የሚጸለይ ቢኾንም ምዕመኑን በሥነ-ምግባር በማነጽ ረገድ በዚህ ወቅት የሚሰጠው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተለየ እና እርስ በእርስ መዋደድን፣ መከባበርን እና መደጋገፍን ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ራሱን ለፈጣሪ የሚያስገዛ ሰውነትን ለመገንባት አጋዥ ነው ያሉት መምህሩ ወደ ፈጣሪ የሚቀርብ ሰው መጀመሪያ ማክበር ያለበት ወንድሙን ነው በሚል አስተምህሮ የሚሰበክበት እና የሚተገበርበት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በሰፊው ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት የሚሰበክበት ነው። ይህ ደግሞ ከግለሰብ አልፎ ለማኅበረሰብ እና ለሀገር ሰላም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን የምንኖርበት ዓለማዊ ሕይዎት በርካታ ችግሮች የሚስተናገዱበት ቢኾንም ምዕመናን በመንፈሳዊ ሕይዎት የሚያገኙትን በረከት በማሰብ ለመልካም ሥራ የሚተጉበት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶችም በዚህ በኩል ኀላፊነታቸውን ይወጣሉ ነው ያሉት፡፡ ምዕመናን በዚህ ወቅት ሃይማኖታዊ አስምህሮውን እና ቤተ ክርስቲያን የምትሰብከውን ሰላም በመተግበር ለአካባቢያቸው እና ለሀገራቸው ሰላም እንዲተጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን