“የገዘፈ ታሪክ ባለቤቶች፤ የአሸናፊነት ወላጆች”

22
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የገዘፈውን ታሪክ በገዘፈ ስብዕና ጽፈዋል፤ የገዘፈውን ታሪክ በረቀቀ ጀግንነት አትመዋል፤ በሚያስደንቅ ብልሃት አኑረዋል።
በጀግንነት አሸናፊነትን ወልደዋል። በጀግንነት ነጻነትን አጽንተዋል። በአንድነት በታሪክ ገናናውን ነገር አድርገዋል። በጥበብ ምንም ቢኾን የማይጠፋውን ታሪክ በወርቅ ቀለም በድንጋይ ብራና ላይ አትመዋል። ከዓለም ዳር እስከ ዳር ለሚገኙ ጥቁሮች ሁሉ መኩሪያ እና መመኪያ ኾነዋል። በጀግንነታቸው የዓለምን አተያይ ለውጠዋል። ጥቁሮች ከድቅድቅ ጨለማ የሚወጡበትን መንገድ ከፍተዋል። መሻገሪያ ድልድዩን አመላክተዋል። መረማመጃ ጎዳናውን አስተካክለዋል።
በጀግንነታቸው የቅኝ ገዢዎችን ዙፋን ነቅንቀዋል። አንገታቸውን አስደፍተዋል። የቅኝ ግዛት ዘመን እያለቀ መኾኑን ማብሰሪያ ደውሉን ደውለዋል። ጥቁር በጀግንነት እና በአንድነት እንደተነሳ፣ ተነስቶም ድል እንደነሳ ነጋሪቱን እየጎሰሙ ለዓለሙ ሁሉ አሰምተዋል። ኢትዮጵያ ላይ ድል ነስተው አውሮፓን አሸብረዋል። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተኝቶ የነበረውን የጥቁር ዓለም አንቅተዋል። በእልህ እና በወኔ አስነስተዋል። እነርሱ እንደ ባል እና ሚስት ስለቤታቸው ይመክራሉ። እንደ ንጉሥ እና ንግሥት በዙፋን ላይ ተቀምጠው ፍርድ ያስተካክላሉ። ለሀገር እና ለሕዝብ የተገባውን ያደርጋሉ። እንደ ጦረኛ ጦር ሜዳ ሄደው ይዋጋሉ፤ ያዋጋሉ። ድልም ይነሳሉ። የሀገርን ዳር ድንበር ያስከብራሉ። ጠላትን ከወሰን ማዶ ይመልሳሉ። ሠንደቅ ዓላማን በአሸናፊነት ከፍ አድርገው ያውለበልባሉ።
እንደ ወላጅ ለሀገራቸው ሕዝብ ሁሉ ይጨነቃሉ። አንድነቱ የሚጠበቅበትን፣ ተድላ እና ደስታ የሚኾንበትን፣ ሰላም እና ፍቅር የሚጸናበትን ዘዴ ሁሉ ይዘይዳሉ። የሮም ጎዳናዎች ይሸበሩላቸዋል። የሮም መኳንንት እና መሳፍንት ያከብሯቸዋል። በአሻገር ኾነው እንጅ ይነሱላቸዋል። የኢትዮጵያ ሊቃውንት ታሪካቸውን ከፍ አድርገው ይናገሩላቸዋል። የተረማመዱባቸው ጎዳናዎች፣ የወጡባቸው ተራራዎች ሳይቀሩ ስለ ከፍታቸው  ይመሰክሩላቸዋል እምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ።
ኢትዮጵያውያን ከፍቅራቸው የተነሳ አጼ ምኒልክን አባት ኾነው ሳለ በእናት ስም ይጠሯቸዋል። እቴጌ ጣይቱን ደግሞ “ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ” የኢትዮጵያ ብርሃን እያሉ ያወድሷቸዋል። በዘመናቸው ተግባብተው እና ተዋድደው የሀገርን ነጻነት አጽንተዋል። የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ጠብቀዋል። የኢትዮጵያውያንን አንድነት አደርጅተዋል። ለሀገሩ በአንድ የነጋሪት እና የመለከት ድምጽ ከዳር ዳር እንዲሰባሰብ አድርገዋል። ሁሉም ነገር ከሀገር እና ከሠንደቅ በታች እንደኾነ አስተምረዋል። ለሀገር እና ለሠንደቅ ሕይዎቱን የማይሰስት ትውልድ ገንበተዋል።
እነዚህ በታሪክ የገነነ ስም ያላቸው ንጉሥ እና ንግሥት ልደታቸው በአንድ ቀን ነው። የሀገሬው ሰው ባል እና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ ይላል። የእነርሱ ግን ከዚያም ያለፈ ይመስላል። ልደታቸው በአንድ ቀን ነውና። ምንም እንኳን በተመሳሳይ ዓመተ ምህረት ባይወለዱም የባል እና ሚስቱ የልደት ቀን ግን የተገጣጠመ ነው። ይህም ሀገሬውን ሁሉ ያስደንቃል፤ ያስገርማልም። እነኾ ልደታቸው ዛሬ ነው። የኢትዮጵያን ታላቅነት ያሰበ ሁሉ ንጉሡ እና ንግሥቷን ያስባቸዋል። በዓድዋ ታሪክ የሚኮራ ሁሉ በንጉሥ እና በንግሥቷ፣ እነርሱም በመሩት ሕዝብ ሁሉ ይኮራል። የኢትዮጵያን ዘመናዊነት ያስታወሰ ሁሉ ንጉሡን እና ንግሥቷን ያስታውሳቸዋል። የልደታቸውን ቀን ያስብላቸዋል። የከበረውን ታሪክ ያከብርላቸዋል።
እምዬ ምኒልክ እና ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ውልደታቸው በነሐሴ 12 ቀን ነው። ቀኝ አዝች ታደሰ ዘወልዴ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አጭር የሕይወት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው እቴጌ ጣይቱ በነሐሴ 12/1832 ዓ.ም በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር ተወለዱ፡፡ ተጠምቀው ክርስትና የተነሱት በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ነው ብለዋል። የንጉሥ ምኒልክ ልደትም ከዓመታት በኋላ ከባለቤታቸው ልደት ጋር የገጠመ ነው። ተክለጻድቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተነሰኘው መጽሐፋቸው ምኒልክ በነሐሴ 12/1836 ዓ.ም አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ተወለዱ። ከአባታቸው ከንጉሥ ኃይለ መለኮት እና ከወይዘሮ እጅጋየሁ ጋር በአንጎለላ፣ በአንኮበር እና በደብረ ብርሃን አድገዋል ብለው ጽፈዋል፡፡
ጳውሎስ ኞኞም አጤ ምኒሊክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ምኒልክ ነሐሴ 12/1836ዓ.ም ቅዳሜ ዕለት ተወለዱ በማለት መዝግበዋል፡ አባታቸው ኃይለ መለኮት ሣሕለ ሥላሴ፣ እናታቸው ደግሞ እጅጋየሁ ለማ ይባላሉ። ምኒልክ ከመወለዳቸው አስቀድሞ ትንቢት የተነገረላቸው፡፡ ጠቢባን እና ደጋግ ሰዎች የመዳረሻቸውን ነገር አስቀድመው ያዩላቸው ሰው እንደነበሩ ይነገራል፡፡ እቴጌም ቢኾኑ በልጅነት ዘመናቸው ለታላቅ ነገር የታጩ ነበር ይባላል። ቀኝ አዝች ታደሰ ዘወልዴ የጀግና ልቦና ለሀገሬ እንጂ ለራሴ ከሚል ግላዊ ሃሳብ የራቀ ነው፡፡ የዕድለኛይቱ፣ የታሪከኛይቱ እቴጌ ጣይቱ ልቦና ለሀገሬ ማለትን ከሁሉ ያስቀድም ነበር ይላሉ።
አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ተደጋግፈው በጦሩም በሰላሙም ጊዜ እኩል በመኖር እቴጌ የእህት፣ የሚስት እና የንግሥትነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ አድርገዋል፡፡ እቴጌ ጣይቱ የአጼ ምኒልክ ሚስታቸው ከመኾናቸውም በላይ እንደ እህት ኾነዋቸው ማንኛውንም ነገር ያማክሯቸው፣ ያበረታቷቸው እና ያጥናኗቸው ነበር፡፡ ንጉሥ ብለው ነበር የሚጠሯቸው፡፡ አጼ ምኒልክም ይወዷቸው እና ያከብሯቸው ነበር፡፡ ታላላቅ ውሳኔዎችን ሲወስኑ ተመካረው ይወስኑ ነበር ብለው መዝግበዋል።
እኒህ በአንድ ቀን ልደታቸውን የሚያከብሩት፣ ለአንድነትም ዘመናቸውን የሰጡት፣ በአንድነትም የሚታወቁት ንጉሥ እና ንጉሥት ዘመናቸውን የተሳካ ነበር ይባልላቸዋል። ሐሪ አትክንስ የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ምኒልክ ተስፋ የሚጣልባቸው ጦረኛ፣ ጥበበኛ መሪ፣ በማስተዳደር ችሎታም ኾነ ፍጹም የኾነ ግዳጃቸውን ፈጽመዋል፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ የአርቆ ማሰብ ችሎታ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ቁጥጥር ሥር እንዳትገባ አድርጓል ብለው ጽፈዋል። ከምኒልክ ጀግንነት እና ብልሃት ጋር ደግሞ እቴጌ አሉ።
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው አጼ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን ካገቡ በኋላ ቤተ መንግሥቱ ግርማና ውበት ተጫነው። ጥላው ከበደ የእውነተኛው አዱኛ፣ የእውነተኛው ደስታ ከጣይቱ ብጡል ጋራ ገባ። እቴጌ ከጣይቱ እጣይቱ ለመባል ይገባቸዋል። እንደ እውነትም ጣይቱ ብጡል ከገቡ በኋላ ያባ ዳኘው መንግሥት ወድያው እያደረ ሰፋ። ተሳፋ፣ ገነነ፣ ተጋነነ፣ ከሞገሥ ሞገሥ ከግርማ ግርማ ጨመረ ብለዋል።
እቴጌ ጣይቱ ብጡል የምኒልክን አልጋ በምክር ሲደግፉ፣ በጕልበት ሲያጠኑ ኖረዋል። እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንደ ሌሎች ሁሉ ንግሥቶች አይደሉም። የመከሩት ሀገር የሚያሳድር፣ የተናገሩት ከምድር ጠብ የማይል ለባለቤታቸው መልካም ደጋፊ፣ ለኢትዮጵያ ጋሻ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ የጣይቱን ወረታ አታጠፋም ብለው ጽፈዋል። እኒህ ብልህ ንጉሥ እና ንግሥት ዓድዋን የመሰለ ድል ለኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያውያን እና ለጥቁር ዘር ሁሉ አበርክተዋል። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የበዙ የሥልጣኔ መሠረቶችን ጥለዋል። ነጻነት የዘላለም ውርስ ይኾን ዘንድ በቃል ኪዳን አሥረው ሰጥተዋል።
ሐሪ አትክንስ ሲጽፉ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘ ድርጊት ከመኾኑ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለው የቆዬ የነጻነት ፍቅር አርማ ሊኾን በቅቷል፡፡ በዓድዋ ምክንያት ጣልያኖችም የወጫሌ ውል መደምደሚያ የኾነውን ኢትዮጵያ አንድ ታላቅ ነጻ ሀገርነቷን በማወቅ ከኢትዮጵያ ጋር የሰላም ውል ተዋዋሉ ብለው መዝግበዋል። ታላቁ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም ካርታ ከማጉላቱ ጋር እነኾ በቀላል ቀኝ ለመኾን የማትበገር አፍሪካዊት ሀገር መኾኗን አስመስክሯል፡፡ ከዓድዋ ጦርነት በኋላ በውጭ ሀገራት ላይ ያደረው ኢትዮጵያን የማወቅ ፍላጎት አዲስ አበባን በጥቂት ጊዜ ውስጥ በአምባሳደሮች ሊሞላት ምክንያት ኾኗል ይላሉ።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983ዓ.ም በተሰኘው መጽሐፋቸው በቅርብ ዘመን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዝናን የሰጠ ድርጊት ማሳብ ያደጋታል፡፡ የቅኝ አገዛዝን ማዕበል የገታ አንድ ትልቅ ደርጊት እንደመኾኑ ሁሉ የቅኝ ገዢዎችን ቅስም የሰበረውን ያክል የተገዢዎችን አንገት ደግሞ ከተደፋበት ቀና እንዲል ያደረገ ክስተት ነበር፡፡ በዚህ ድል ምክንያትም የፖለቲከ መሪዎችም ኾኑ ነጋዴዎች አቋማቸውን እንደገና እንዲመረምሩ ተገደዱ ብለው ጽፈዋል፡፡
ፕሮፌሰር ባሕሩ ጆርጅ ብርክሌን ጠቅሰው ሲጽፉ ከሰፊው የፖለቲካ እና የታሪክ ትንታኔ አኳያ የዓድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድር አዲስ ኃይል መነሳቱን የሚያበስር ይመስላል፡፡ የዚያች አህጉር ተወላጆች የማይናቁ ወታደራዊ ኃይል ሊኾኑ እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል፡፡ ዓድዋ ጨለማይቱ አህጉር በላይዋ ላይ ሥልጣኗን ባንሠራፋችው በአውሮፓ ላይ የምታደርገው አመጽ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡
ዓድዋን ልዩ ትኩረት ያሰጠው ጥቁሮች በነጮች ላይ የተጎናጸፉት፣ የመጀመሪያው ዐቢይ ወታደራዊ ድል በመኾኑ ነው፡፡ የዓድዋ አብነት በተለይም የነጮች የበላይነት አስከፊ የዘር መድሎ ፖሊስ ጋር በተቆራኘባቸው የላቀ ነበር፡፡ በነጮች መድሎ ሥር ለነበሩ ሀገራት ኢትዮጵያ የነጻነት እና የክብር ፋና ወጊ ኾነች፡፡ ቀድሞውን ቢኾን በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያኒዝም እየተባለ ለሚጠራው ከነጮች ተጽዕኖ ነጻ የኾነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ መንስኤ ሆና ነበር ተብሎ ተጽፏል።
ኢትዮጵያን ያኮራችሁ። የተቸገሩትን ያስጠለላችሁ። ለጥቁር ዘር ሁሉ መመኪያ እና መኩሪያ የኾናችሁ፣ ነጻነትን በጽኑ መሠረት ላይ ያጸናችሁ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ያይረጃችሁ ንጉሥ እና ንግሥት ኾይ ልደታችሁ ሲያሰብ አንድነት ይታሰባል። ልደታችሁ ሲታወስ ነጻነት ይታወሳል። ልደታችሁ ሲዘከር የኢትዮጵያ ታላቅነት እና ኃያልነት ይዘከራል። ለሀገር ታላቁን ገድል ተጋድላችኋልና እንኳን ተወለዳችሁ። የገዘፈ ታሪክ ባለቤቶች፣ የአሸናፊነት ወላጆች ናችሁና ኢትዮጵያም ውለታችሁን አትረሳም።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበ25 ዓመታቱ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ ሥራ አጥነትን መቀነስ ዓብይ ተግባር ነው።
Next article“ፍልሰታ ለሀገር ሰላም”