በ25 ዓመታቱ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ ሥራ አጥነትን መቀነስ ዓብይ ተግባር ነው።

25
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት የክልሉን እድገት ለማረጋገጥ የ25 ዓመታት አሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ቀርጾ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
ይህ የዘላቂ ልማት ዕቅድ ለሥራ አጥነት ቅነሳ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቷል በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ኀላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ዶክተር ደመቀ በዓለም ሀገራት የዕድገት መመዘኛዎች መሠረት የአንድ ሀገር መንግሥት ጸንቶ የሚኖረው ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ የኑሮ ውድነትን ማስተካከል እና ዕድገት ማረጋገጥ ሲችል ነው ብለዋል።
ለሥራ የደረሱ ዜጎች ወደ ሥራ እስካልተሰማሩ ድረስ የሀገር ዕድገትን ብሎም የክልል ሁለንተናዊ ለውጥ ማረጋገጥ አይቻልም፣ ዕድገትን ያላረጋገጠ ሀገር ወይም ክልል ደግሞ ኑሮ ውድነት መቅረፍ አይችልም ነው ያሉት። የአማራ ክልል መንግሥትም የዘርፈ ብዙ ችግሮቹ ምንጭ ሥራ አጥነት መኾኑን አረጋግጧል ነው ያሉት ዶክተር ደመቀ ቦሩ።
አማራ ክልል ከ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሥራ የደረሱ አምራች ዜጎች ያሉት ክልል መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ደመቀ ቦሩ እነዚህ አምራች ዜጎች በአግባቡ ሥራ ላይ እየዋሉ አለመኾኑን አስረድተዋል። ይህንኑ አምራች ኃይል በወቅቱ እና በጊዜው ካልተጠቀምን እያየነው የሚያረጅ፣ ሳንጨብጠው የሚያመልጥ ዕድል ነው ብለዋል። ከዓመታትም በኋላ ይባስ ብሎ ጧሪ እና ቀባሪ የሚፈልግ የሀገር እዳ እንደሚኾን ነው ያብራሩት።
ይህንን በመረዳትም ይላሉ ዶክተር ደመቀ ቦሩ የአማራ ክልል መንግሥት በልዩ ትኩረት ባዘጋጀው የ25 ዓመታቱ የዘላቂ ልማት ዕቅድ ውስጥ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ የተለየ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል። ክልሉ ያለውን የሰው ኃይል፣ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ አቀናጅቶ በመጠቀም ሥራ አጥነትን ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት። ይህ እንዲሳካ ታዲያ በዋናነት የግል ኢንቨስትመንቱን በማበረታታት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈም ግብርናን ማዘመን፣ የከተማ ኢኮኖሚን ማሳደግ፣ የገጠሩን ልማት እና የኑሮ ሁኔታን ምቹ ማድረግ ሥራ አጥነትን ይቀርፋሉ ተብለው በ25 ዓመታቱ የዘላቂ ልማት እቅድ ላይ የተቀመጡ ዓበይት ጉዳዮች መኾናቸውን ዶክተር ደመቀ ቦሩ ጠቅሰዋል። የ25 ዓመታቱ የዘላቂ ልማት ዕቅድ መጀመሪያ በኾነው የ2018 በጀት ዓመትም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ዜጎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
የክልሉ ዕድገት አሁን ካለበት የ5 ነጥብ 1 በመቶ እድገት የዛሬ 25 ዓመት 10 ነጥብ 2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ተተንብይዋል። ይህ ዕቅድ ከሰነድነት ባለፈ መሬት ላይ ወርዶ እንዲተገበር የማስፈጸሚያ ስልቶችም ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት። ልማትን በፍትሐዊነት ማዳረስ፣ ልዩ ፕሮግራሞችን እና ኢኒሼቲቮችን በአግባቡ መጠቀም፣ የማያሠሩ ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን ማሻሻል፣ የተቋማት አደረጃጀቶችን ማስተካከል፣ ክትትል እና ቁጥጥርን ማጠናከር፣ የተግባቦት ስትራቴጂን በውጤታማነት መጠቀም እና የኅብረተሰብ ተሳትፎን ማረጋገጥ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ለሚሠሩ ሥራዎች የማስፈጸሚያ ስልቶች ናቸው ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ደመወዝ የቆዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ለድህነት ተኮር ዘርፎች ከጥቅል በጀቱ 12 ቢሊዮን ብር መድቧል።
Next article“የገዘፈ ታሪክ ባለቤቶች፤ የአሸናፊነት ወላጆች”