
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ2018 በጀት ከ225 ነጥብ 45 ቢሊዮን ብር በላይ ኾኖ በክልሉ ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል። ይህ በጀት ድህነት ተኮር ሴክተሮች ተብለው ለተለዩ ተቋማት ልዩ ትኩረት እንደሚሠጥም ተገልጿል።
ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ውኃ እና መንገድ ድህነት ተኮር ሴክተሮች ተብለው የተለዩ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት ድህነት ተኮር የተባሉበት ምክንያት ዜጎች በስፋት መሠረታዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙባቸው በመኾናቸው ነው ይላሉ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አታላይ ጥላሁን። አቶ አታላይ እንዳሉት በ2018 በጀት ዓመት የድህነት ተኮር ሴክተሮች እንደማንኛውም ተቋም በመደበኛነት ከሚመደብላቸው በጀት ሌላ ከጥቅል በጀቱ 12 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ተመድቦላቸዋል ብለዋል።
የክልሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በዋናነት የተሸከመው ግብርና በመኾኑ የግብርና ዘርፎችን ለማሻሻል እና ለማዘመን ከ12 ቢሊዮኑ ጥቅል ገንዘብ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነውን ድርሻ እንደሚወስድ አቶ አታላይ ተናግረዋል። የክልሉ የኢኮኖሚ እድገት ማሳለጫ የኾነው መንገድም 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድርሻ እንዳለው የገለጹት አቶ አታላይ የትምህርት ግብዓቶችን ለማሟላት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር፣ የውኃ ተደራሽነት ለማሳደግ 2 ቢሊዮን ብር እና የጤና አገልግሎትን ለማስፋፋት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ድርሻ እንዲኖራቸው ተደርጓል ብለዋል።
በጀቱ ለታለመለት ዓላማ ይውል ዘንድ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ የፋይናንስ ተቋማቱ ሰፊ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ መዘጋጀቱን አቶ አታላይ ገልጸዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ለድህነት ተኮር ሴክተሮች የተመደበው ገንዘብ ችግር ፈቺ ይኾን ዘንድ ልዩ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሃናን አብዱ ገልጸዋል። ሰብሳቢዋ የክልሉ ማኅበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውኃ ገና እንደልብ አላገኘም፣ የጤና አገልግሎት ውስንነቱ በበቂ ሁኔታ አልተሞላም፣ የትምህርት ስብራቱ ገና አልተጠገነም፣ የግብርና ዘርፉ የአቅሙን ያህል አለማም፣ የመንገድ መሠረተ ልማት በሚፈለገው ልክ አልተሳለጠም ነው ያሉት። እናም ይላሉ ወይዘሮ ሃናን ማኅበረሰባችን ከእነዚህ ችግሮች እንዲላቀቅ የተመደበው ውስን ሀብት ለታለመለት አላማ እንዲውል በምክር ቤቱ የተቋቋሙት ሰባቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በየሩብ ዓመቱ ስለአፈጻጸሙ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋሉ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ደመወዝ የቆዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን