ችግሮች በሀገራዊ ምክክር ሂደት እንዲፈቱ የሴቶች አስተዋጽኦ የላቀ ነው።

37
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የሴቶች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ከተወከሉ ሴቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድኅን ለሀገራዊ ችግሮች በጋራ ሀገራዊ መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ምሁራንን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን፣ የማኅበራት አደረጃጀቶችን እና ሌሎችንም አካላት ወደ አንድ በማሠባሠብ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በርካታ ጥረቶች እያደረገ መኾኑን አንስተዋል። የሀገራዊ ምክክሩ ለኮሚሽኑ ብቻ የሚተው ሳይኾን ሁሉም በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አመላክተዋል። ሴቶችም በየአደረጃጀቶቻቸው አማካኝነት በስፋት የሚሳተፉበት ሂደት ነው ብለዋል።
ሴቶች ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ ስለ ሀገራዊ ምክክር መረጃዎችን እስከ ታች ድረስ በማድረስ ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። በክልሉ ለተከሰተው ግጭትም መፍትሔ ለማምጣት እና ችግሮች በሀገራዊ ምከክር ሂደት እንዲፈቱ ለማድረግ የሴቶች አስተዋጽኦ የላቀ ነው ብለዋል። ሴቶች በግጭት እየተሳተፉ ያሉ አካላትን ወደ ሰላም የማምጣት አቅም እንዳላቸውም ጠቁመዋል። ምክክሩ ሙሉ እንዲኾን እና የሕዝብ ባለቤትነት እንዲጠናክር ሴቶች ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በቀጣይ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት የሴቶች ሚና ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል። የውሳኔ ሃሳብ በማመንጨት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።ሴቶችን ለማብቃት እና በሀገራዊ ምከክር ሂደት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መኾኑም ተገልጿል። በመድረኩ ላይ በርካታ ሀሳብ እና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ዘጋቢ፦አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአፈር ማዳበሪያ እና የጸረ ተባይ ኬሚካል ስርጭት መመሪያ ወጣ፡፡
Next articleመንግሥት የመንግሥት ሠራተኞችን የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል የሚያስችል አዳዲስ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ።