
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ቁጥጥር ባለሥልጣን በአፈር ማዳበሪያ እና ጸረ ተባይ ኬሚካል አሥተዳደር መመሪያዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ቁጥጥር ባለሥልጣን ከሚሠራቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ የግብርና ግብዓት በጥራት ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ማድረግ ነው ያሉት የአማራ ክልል የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኀላፊ ፈንታሁን ስንታየሁ ናቸው፡፡ ተቋሙ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ በሚቀርብበት ጊዜ በተቀመጠለት አሠራር እና ሥርዓት አርሶ አደሩ በቀላሉ መንገድ አግኝቶ የሚፈለገውን ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛውን ሚና የሚጫወት ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ እንደ ክልል በማዳበሪያ እና በጸረ-ተባይ ኬሚካል ስርጭት ላይ ራሱን የቻለ መመሪያ አልነበረም ነው ያሉት፡፡ መመሪያው ባለመኖሩ ምክንያት የአፈር ማዳበሪያ በአግባቡ የሚሰራጨው እንደተጠበቀ ኾኖ በሕገ-ወጥ መንገድም ከፍተኛ የኾነ የስርጭት እንቅስቃሴ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ በተለይ የሌለ ውጥረት በመፍጠር ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ በማሳየት፣ ለአርሶ አደሩ በአግባቡ እንዳይቀርብ የማድረግ ችግሮች ሲፈጠሩ ቆይተዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት መጀመሪያ የአፈር ማዳበሪያ እና የጸረ-ተባይ ኬሚካል ስርጭት አሠራር እና ቁጥጥር መመሪያ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡ይህም የነበረውን ችግር ሊፈታ የሚችል፣ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መመሪያ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ይህን መመሪያ በተጨባጭ ሥራ ላይ በማዋል ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል ነው ያሉት፡፡ በዚህም የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት በመጨመር በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
አርሶ አደሩም ከሕገ-ወጦች ነጻ በኾነ መንገድ በመመሪያው መሠረት ማዳበሪያ መንግሥት በሚያቀርብለት አግባብ ይወስዳል፤ ጸረ ተባይ ኬሚካሉንም በአግባቡ ይጠቀማል ነው ያሉት፡፡እንደ ኀላፊው ገለጻ መመሪያወችን ማውጣት ብቻ ሳይኾን ወደ ተግባር ገብቶ ተፈጻሚ እንዲኾኑ ማድረግም እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡ለዚህም የፍትሕ አካላት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና የግብርና ተቋሞች መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ጉልህ ሚና ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በግብርናው ላይ ነው፤ በዚህ ዘርፍም ከፍተኛ የኾነ ለውጥ እና ዕድገት ማምጣት ይጠበቅብናል ያሉት የግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ናቸው፡፡ይህንን ለውጥ ለማምጣት ደግሞ የግብዓት አቅርቦት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ያለ ቴክኖሎጅ እና ያለ ግብዓት የሚጨምር ምርትም የሚዘምን ግብርናም የለም ያሉት ምክትል ኀላፊው ከግብዓት መካከል በስፋት የሚቀርበው የአፈር ማዳበሪያ ነው፡፡
እስካሁን ባለው 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት ተችሏል፡፡
በዚህ ወቅት በዝውውር እና በስርጭት ላይ የሚፈጠሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች አሉ ብለዋል፡፡ ማዳበሪያን ማዘዋወር የሚችሉት መንግሥት የወከላቸው የመንግሥት ተቋማት ብቻ ኾነው እያለ ሕገ ወጥ ነጋዴው የአፈር ማዳበሪያ ክምችት እና ዝውውር ሲያደርግ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡ ይህ ሁኔታ ባለበት ከዚህ በፊት እነሱን በሕግ አግባብ የሚያስጠይቅ የወጣ ድንጋጌ አልነበረም፡፡ በዚህም በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ ቢገኙም በሕግ ለመጠየቅ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል፡፡ዛሬ ውይይት የተደረገበት የሕግ ድንጋጌ የአፈር ማዳበሪያ ማቅረብ እና ማሰራጨት ያለባቸው ተቋማት እነማን ናቸው የሚለውን በግልጽ ይደነግጋል፤ በራሳቸው አከማችተው የሚሸጡ ግለሰቦችንም በሕግ ተጠያቂ ያደርጋል ነው ያሉ፡፡
ይህ ድንጋጌ ሕገ ወጥ አሠራርን በመቅረፍ በኩል በእጅጉ ያግዛል ብለን እናምናለን ያሉት ምክትል ኀላፊው ይህ የተሳካ እንዲኾን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡የክልሉ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የግብዓት እና ግብይት ዳይሬክተር ዓለም ዘውድ ስሜነህ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እና ቁጥጥር የወጣው መመሪያ እንደባለድርሻ አካላት የራስን ሚና በአግባቡ ለመወጣት ያስችላል ነው ያሉ፡፡ ከ99 በመቶ በላይ የሚኾነው በክልሉ የሚቀርበውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የሚያሰራጨው ማኅበራት ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ አሁን የወጣው መመሪያ ማን በጅምላ ያከፋፍላል፣ ማን በችርቻሮ ያቀርባል የሚለውን በግልጽ ያስቀመጠ መመሪያ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ መመሪያው በትክክል አርሶ አደሩን በመለየት ለሚያስፈልገው መሬት የሚያስፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ አረጋግጦ የሚሰጥ ኀላፊነት የተሰጠው አካል መኖሩንም በግልጽ ያመላከተ በመኾኑ ፋይዳው የላቀ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ በሥልጠናው የግብርና ቢሮ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ከፍያለው ሙላቴ፣ የግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው እና የሚመለከታቸው አካላትም ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!