
ደብረ ታቦር፡ ነሐሴ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩም በትምህርት ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተው በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። ከዳግማዊ አጼ ቴዌድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት የመድረኩ ተሳታፊ ጓዴ አየነው ባለፉት ዓመታት በከተማው ያሉ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሂደቱን ቢያስቀጥሉም በገጠር ቀበሌዎች ሙሉ እንዳልነበር ተናግረዋል።
በአዲሱ የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው በወቅቱ እንዲገኙ በሃይማኖት እና መሰል ተቋማት ቅስቀሳ ለማድረግ በዕቅድ እየተሠራ ነው ብለዋል። ትውልድን ወደቀጣይ ለማሸጋገር የትምህርት ሚና ወሳኝ ነው ያሉት ከዳግማዊ ቴዎድሮስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት የመድረኩ ተሳታፊ ርእሰ መምህር ሽዋንግዛው ታየ ትምህርት ላይ በትኩረት መሥራት የሀገር ዕድገት መሠረት ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ለ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የምዝገባ ጊዜ በተደራጀ መልኩ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ሥራ መገባቱንም ነው የነገሩን። በምዝገባ ንቅናቄው ላይ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ሀገር በትምህርት የበለፀገ ትውልድ ከሌላት ትውልድን ማስቀጠል አይቻልም ያሉት የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ ናቸው። መምሪያ ኀላፊው የነገ የሀገሪቱ መልክ የሚወሰነው በዛሬ ተማሪዎች ነውም ብለዋል። በመኾኑም ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። የቀጣይ ብቁ ትውልድ ርክክብን ለማስቀጠል ትልቅ ችግር ገጥሞናል፤ ለችግሩ የመፍትሔ ሰዎች በመኾን ተማሪዎችን በትምህርት ገበታቸው እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ለሚጀመረው የምዝገባ ሥራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።አቶ እየበሩ ሁሉም የድርሻውን በመወጣት ለትምህርት የደረሱ ሁሉ በትምህርት ገበታቸው እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን ባለፉት ሁለት ዓመታት የትምህርት ዘመን በከተማ አሥተዳደሩ የነበረው የትምህርት ሂደት በስኬት እንዲቀጥል የመሪዎች እና የማኅበረሰቡ ክትትል እና ድጋፍ አይተኬ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል። የውጤታማ መማር ማስተማር ሂደት ወሳኙ ጉዳይ የተማሪዎች ምዝገባ መኾኑን ያነሱት አቶ ደሴ የትምህርት ሥራውን በተሻለ መንገድ ለማስኬድ ሁሉም ኀላፊነትን ወሶዶ እንዲሠራ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!