
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለመጅሊስ በተዘጋጀው ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የዑላማዎች ምርጫ የተካሄደ መኾኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ ቦርድ ጸሐፊ እና የሰሜን ክላስተር ቡድን መሪ ሼህ ሙሐመድ ጦይብ አስታውቀዋል።
ምርጫው በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በተዋረድ ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት እና ብቁ መሪዎችን ወደፊት ለማምጣት የተካሄደ ነው ብለዋል።ዛሬ ለምርጫ እጩ ኾናችሁ የቀረባችሁ ዑላማዎች የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ጥያቄ የምትመልሱ፣ ተተኪውን ትውልድ የምትገነቡ እና በታማኝነት አገልጋይ የምትኾኑበት አደራ ነው የሚጣልባችሁ ብለዋል ሼህ ሙሐመድ ጦይብ።
ይህንን አደራ ለመወጣት ያላችሁን የውስጥ ብቃት በመጠቀም ለማገልገል ራሳችሁን ዝግጁ ያደረጋችሁ መኾን አለባችሁም ብለዋል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ጀውሐር ሙሐመድ ኢሳ ይህ ምርጫ ሕዝበ ሙስሊሙ ይመራኛል፣ ያሥተዳድረኛል እና ያገለግለኛል የሚለውን ሰው ወደፊት ለማምጣት የተደረገ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
“እኔ ለሦሥት ዓመት ያህል በሹመት የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆኘ አገልግያለሁ፤ አሁን ደግሞ ለሕዝበ ሙስሊሙ ለማገልገል እራሴን በተመራጭነት አቅርቤያለሁ፤ ይህ ምርጫ በዑላማወች መኾኑ ለተቋማዊ ግንባታ ያለው ፋይዳ ወሳኝ ነው” ብለዋል። ማኅበረሰቡም በመሪው እንዲተማመን፣ ፍትሐዊ ለመኾን እና አብሮ ለመሥራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት። ይህ በመኾኑም ደስተኛ እንደኾኑ አብራርተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ መሥተዳደር እስልምና የደዕዋ ዋና የትምህርት ክፍል ኀላፊ አብዱል ሀዚዝ ሀሰን ምርጫው ፍትሐዊ እንዲኾን አቅም እንደፈቀደ ብቃት አላቸው፣ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በፍትሐዊነት ይመራሉ ያሏቸውን ሰዎች እንደመረጡ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በውስጥ ትውውቅ ነበር ኀላፊነት የሚሰጠው፤ አሁን ግን ማኅበረሰቡ የሚወክለውን እንዲመርጥ የተሰጠው ዕድል ቀላል አይደለም፤ ይህም ከዚህ በፊት የነበሩ አለመግባባቶችን ይፈታል ብየ አምናለሁ ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ 33 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ። በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የዑላማዎች ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል ያሉን ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምርጫ ቦርድ አሥፈፃሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ሐጅ አብዱል ከሪም ሀሰን ናቸው። በዚህ ምርጫ በሁሉም ዘርፎች ከ11ሺህ በላይ መራጮች ይሳተፋሉ። የአሁኑ ምርጫ በየ ዘርፉ መኾኑ ብቃት ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
“ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ኅብረተሰቡ መጅሊሱ አይወክለኝም የሚል እሳቤ ነበረው አሁን የተሰጠን ዕድል መልካም አጋጣሚ ነው” ሲሉ ጠቁመዋል። ይህንን ዕድል ተጠቅመን የተሻሉ ሰዎችን ለመምረጥ ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም በሚኖረው አጠቃላይ ምርጫ መራጩ ሰዓቱን አክብሮ በመገኘት ምርጫ እንዲመርጥ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!