በግጭት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ ነው።

23
ደሴ: ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በግጭት ለተጎዱ ሕዝቦች የኢኮኖሚ መልሶ ማቋቋም የተሰኘው ፕሮጀክት በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በኢኮኖሚ እንዲያገግሙ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ ከአሁን ቀደም በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ እና በአፋር ክልል አብአላ ወረዳ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የገለጹት የፕሮግራሙ አስተባባሪ ትዕግሥት ብሩክ በአማራ ክልልም በወልድያ ከተማ አሥተዳደር ፕሮጀክቱን ለመተግበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱን በወልድያ ከተማ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
የፕሮግራሙ አስተባባሪ ትዕግሥት ብሩክ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና በግብርና ሥራዎች በመሳተፍ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል። በተጨማሪም የሥነ ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፎችን በመስጠት በጦርነቱ የተጎዱ አነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማትን ወደ ሥራ የመመለስ እና ሌሎች የብድር አገልግሎቶችም ይቀርባሉ ነው ያሉት።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ንጉሥ ዝናቡ በአካባቢው በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ክስተቶች በርካታ ወገኖች ለጉዳት መዳረጋቸውን ገልጸው ፕሮግራሙ ተጎጅዎች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስረድተዋል። ተጎጅዎችን በአግባቡ በመለየት ፕሮጀክቱ ዓላማውን እንዲያሳካ ለማድረግ ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲደረግ የመሥሪያ ቦታ እና የገንዘብ አቅርቦት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ይሠራል ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ክትትል እና ግምገማ ባለሙያ ሙሉጌታ መኩሪያው ናቸው። ገንዘቡን ከባንኮች ጋር ትስስር በመፍጠር በተዘዋዋሪ የብድር አገልግሎት እንዲጠቀሙ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ምሳዬ መኮንን ፕሮጀክቱ ለችግር የተጋለጡ ወጣቶች እና ሴቶች ላይ በልዩ ትኩረት ስለሚሠራ የመንግሥትን ጉድለት እንደሚሸፍን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ለታለመላቸው ወገኖች በትክክል እንዲደርስ በምልመላ እና መረጣ ሥራው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleእየተጠበቀ ያለው የትራምፕ እና የፑቲን ምክክር
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የዑላማዎች ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ።